ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ ሲደርስ ግማሹ አገገሙ
በዓለም ዙሪያ በፍጥነት እየተስፋፋ ባለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ ደረሰ።
በሽታው ከቻይና ውጪ ወደ ሌሎች አገራት መዛመት ከጀመረ ስድስት ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም የመከላከያ ክትባትም ሆነ የሚፈውስ መድኃኒት ሳይገኝለት በየዕለቱ በዓለም ዙሪያ በ10 ሺህዎች እየተያዙ ይገኛሉ።
አስከ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ ያለው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሃዝ እንደሚያመለክተው 11 ሚሊዮን 074 ሺህ 878 ሰዎች በዓለም ዙሪያ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።
ይህ ቁጥርም አገራት በዜጎቻቸው ላይ እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው ምርመራን ተከትሎ በየደቂቃው እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን፤ የበሽታው የመዛመት ፍጥነትም እየጨመረ መሆኑን ባለሙያዎች ይረናገራሉ።
በዓለማችን በበሽታው መያዛቸው ከታወቁት ከ11 ሚሊዮን ከሚበልጡት ሰዎች መካከል ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው ህሙማን የሚገኙት አሜሪካ ውስጥ ሲሆን ቁጥራቸውም 2 ሚሊዮን 794 ሺህ 153 ነው።
በሁለተኝነት ደግሞ ብራዚል 1 ሚሊዮን 539 ሺህ 081 በበሽታው የተያዙ ሰዎች እንዳገኘች ያረጋገጠች ሲሆን ሩሲያ ደግሞ በ666 ሺህ 941 ህሙማን ሦስተኛዋ አገር ሆናለች።
በሽታው የተረጋገጠ ፈዋሽ መድኃኒት ባይኖረውም በርካቶች በተለያዩ መንገዶች ከበሽታው ማገገማቸው ታውቋል።
የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ እንደሚያመለክተውም እስካሁን በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡት ከ11 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ማገገማቸውን ያመለክታል።
በዚህም መሰረት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ 5 ሚሊዮን 863 ሺህ 847 ሰዎች በዓለም ዙሪያ ከወረርሽኙ ያገገሙ ሲሆን ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበባት አገር ደግሞ ብራዚል ናት።
በብራዚል 984 ሺህ 615 ሰዎች፣ በአሜሪካ 790 ሺህ 404 ሰዎች እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ሩሲያ ውስጥ 437 ሺህ 115 ሰዎች ከኮሮናቫይረስ አገግመዋል።
በተጨማሪም በበሽታው ሰበብ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 525 ሺህ 121 ሰዎች በዓለም ዙሪያ ህይወታቸውን ሲያጡ፤ ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገቡባት አገር አሜሪካ ናት።
በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ ሰበብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 129 ሺህ 434 ሆኖ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ስትገኝ በሁለተኛዋ ብራዚል ውስጥ ደግሞ 61 ሺህ 884 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ሦስተኛዋ አገር ደግሞ ዩናይትድ ኪንግደም ስትሆን የሟቾች ቁጥር 44 ሺህ 216 ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት በየዕለቱ በሚያወጣው መረጃ መሰረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።