ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማድረግ ያለብን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ምን ዓይነት ነው?
ከሰሞኑ የመተንፈሻ ቀዳዳ ወይም ቫልቭ የተገጠመላቸው (በተለምዶ N95) የሚባሉ ማስኮች በሽታ ለመከላከል የሚውሉ እንዳልሆኑ የመድሃኒትና ምግብ ባለሥልጣን አስታውቋል።
በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብደላ ካሶ እነዚህ የአፍና የአፍንጫ ማሸፈኛዎች በተለይ ይህንን በሽታ የሚያባብሱ እንጂ ጥቅም የሚሰጡ እንዳልሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ ማስኮች የሚጠቀመውን ሰው የሚጠብቁና ሌላውን ሰው ግን የሚያጋልጡ "ራስ ወዳድ ማስኮች ናቸው" ሲሉም ይገልጿቸዋል።
በመሆኑም ይህንን በሽታ ለመከላከል የሚውሉ የመተንፈሻ ቀዳዳ (ቫልቭ) የሌላቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች በመሥሪያ ቤቱ ተመዝግበውና ተገምግመው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግም ያስረዳሉ።
አቶ አብደላ እንደሚሉት ከሆነ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎቹ ባክቴሪያ ወይም ቫይረስን ከውጭም ሆነ ከውስጥ የማላሳለፍ ብቃታቸው እንዲሁም በአተነፋፈስ ላይ የሚያመጣው ችግር መኖር አለመኖሩን በተመለከተም የጥራት ፍተሻ ይደረግላቸዋል።
የመተንፈሻ ቀዳዳ የተገጠመላቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች ለሌሎች አላማ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በኢንዱስትሪዎች፣ በማዕድን ማውጣትና በመድሃኒት ርጭት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲሁም ስፖርተኞች እንደሚጠቀሟቸው ይገልጻሉ፡፡
N95 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ)
በማህበረሰቡ ዘንድ N95 ተብሎ የተጻፈበት ማስክ በሙሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚከላከል የተሳሳተ አመለካከት አለ። የጥሩ ማስክ መለያውም በላዩ ላይ የተገጠመው የመተንፈሻ ቀዳዳ እንደሆነ ተደርጎ ሲወሰድ ይስተዋላል። አሁን አሁን በርካቶች ከቫይረሱ ራሳቸውን ለመከላከል በስፋት ሲጠቀሙት ይስተዋላል። N95 የሚባለው ማስክ ግን ዓይነቶች እንዳሉት የሚያውቁት ብዙ አይደሉም፡፡
አቶ አብደላ እንደገለጹልን አይነታቸው ሁለት ነው።
- የመተንፈሻ ቀዳዳ የተገጠመላቸው፡ እነዚህ ማስኮች ለህክምና አገልግሎት የማይውሉ ሲሆኑ አገልግሎታቸው ለኢንዱስትሪ እና ሌሎች ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
- የመተንፈሻ ቀዳዳ ያልተገጠመላቸው፡ ባክቴሪያ እና ቫይረስን የማጣራት አቅማቸውም ከ95 በመቶ በላይ የሆኑ፤ እጥረት በመኖሩም የጤና ባለሙያዎች ብቻ መጠቀም ያለባቸው ናቸው። በመጠንም አነስተኛ፣ መካከለኛና ትልቅ ተብለው ለፊት መጠን እንዲመቹ ተደርገው የተዘጋጁ ናቸው። አጠቃቀሙም ሲደረግም ሆነ ሲወገድ ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
የመተንፈሻ ቀዳዳ ያላቸው ማስኮች እንዴት በስፋት ተሰራጩ ?
ዳይሬክተሩ እነዚህ ማስኮች ከዚህ በፊትም ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ እንደነበር ጠቅሰው ለሌሎች አገልግሎቶች አገር ውስጥ ከመግባት አይከለከሉም ይላሉ፡፡
ነገር ግን ወረርሽኙ መከሰቱን ተከትሎ ማስኮቹ በማወቅም ባለማወቅም ለሕብረተሰቡ ሲቀርቡ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቫይረሱ ባህሪውን በመለዋወጡ የዓለም ጤና ድርጅት ማስኮችን በተመለከተ የሚያወጣው የተለያዩ መመሪያዎች አገልግሎት ላይ እንዲሆኑ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ይወጡ እንደነበር የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ማንኛውም ሰው ማስክ እንዲጠቀም የሚያስገድደው አዋጅ ከወጣ በኋላ፤ ሕብረተሰቡ መጠቀም ያለበትን ማስኮች ምንነት ለማሳወቅ መመሪያውን እንዳወጡ ይገልጻሉ፡፡
አሁንም እነዚህ ማስኮች ለበሽታ መቆጣጠርና መከላከል እንደማይውሉ ከማስተማር ውጭ ዞሮ መሰብሰብም ሆነ ለሌላ ጥቅም የሚውሉ በመሆናቸው ማስኮቹ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡
በእርዳታ የሚገቡ ማስኮችም በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ታይተው ፈቃድ የተሰጣቸውና በሽታውን ለመቆጣጠር የሚውሉ እንደሆኑ አስምረው ተናግረዋል፡፡
ሰዎች ማስክ ሳያደርጉ ከሚንቀሳቀሱ ከጨርቅ የተሰሩ ማስኮችን ማድረግ ይበጃል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ማስኮች የተከለከሉት የሚያደርገውን ሰው ከበሽታው ጠብቆ ሌላውን ሰው የማይጠብቁ በመሆናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቲቢን ጨምሮ ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መደረግ ያለበትም የመተንፈሻ ቀዳዳ የሌላቸውን መሆን አለበት፤ መተንፈሻ ቀዳዳ ያላቸውን ከመጠቀም ይልቅ ሻሾችን ስከርፖችን ቢጠቀሙ ይመከራል ይላሉ- አቶ አብደላ፡፡
ትክክለኛ ማስኮች የትኞቹ ናቸው?
ሕብረተሰቡ ከበሽታው ራሱን ሌሎችን እንዲጠብቅ ተገቢ ማስኮችን እንዲጠቀም እያስተማሩ እንደሆነ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የጨርቅ ማስኮች ከ70 በመቶ በላይ ጥራት እንዲኖራቸው የሚያስችል፣ እንዴት ይመረቱ? ይታሸጉ? ይሰራጩ? በሚል መመሪያ ወጥቶ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት መሰራጨቱን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ፡-
- የመተንፈሻ ቀዳዳ ያልተገጠመላቸው የህክምና ማስኮች
- በቤት ውስጥ የሚመረቱ ከሆነም በማን እንደተመረቱ የሚታወቁና ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ
- ለንክኪ ያልተጋለጡ ወይም የታሸጉ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ አጠቃቀሙንና አወጋገዱን በተመለከተም ከጤና ሚኒስቴር የሚነገሩ መመሪያዎችን መከተል እንደሚገባ አቶ አብደላ አሳስበዋል፡፡