በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ህሙማን ላይ የአንቲቦዲ ምርመራ መደረግ ተጀመረ

በኢትዮጵያ ከኮቪድ-19 አንጻር ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል ህዋሳት (አንቲቦዲ) ምርመራ በህሙማን ላይ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ሳምንታት እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም አስታወቀ።

ተቋሙ እንዳለው ምርመራው የኮቪድ-19 በሽታ ያለበት ሰው ቫይረሱን ለመለየት የሚረዳ ሳይንሳዊ ሲሆን በተጨማሪም በማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን የበሽታን ስርጭት ለመረዳትና ምላሽ ለመስጠት እንደሚያገለግል ገልጿል።

በተጨማሪም ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑት የኅብረተሰቡ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት ለማወቅ የሚደረገው የአንቲቦዲ ምርመራ አስፈላጊ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል።

ይህ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 15 ድረስ ለሦስት ተከታታይ ሳምንትት የሚካሄደው በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ እየተስፋፋ ባለው ወረርሽኝ በተያዙ ሰዎች ላይ ነው ተብሏል።

ይህ የቅኝት ምርመራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኮሮናቫይረስ በሽታ ስርጭት ለማወቅ የሚያግዝ ሲሆን ምርመራው በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች ውስጥ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ይካሄዳል ተብሏል።

የአንቲቦዲ ምርመራው የሚደረገው ከሰዎች ላይ በሚወሰድ እስከ አምስት ሚሊ ሊትር በሚደርስ የደም ናሙና ላይ ሲሆን፣ የበሽታው ተከላካይ ህዋሳቱ እንደየበሽታው ዓይነት እንደሚለያዩ ተገልጿል።

ይህ ምርመራ የኮሮናቫይረስን ለመካላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው የቅኝት ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተቋሙ አመልክቷል።

አንቲቦዲ አካላችን የሚገጥሙትን የተለያዩ ህመሞች ለመቋቋምና ለመከላከል በተፈጥሮ የሚያዘጋጀው መከላከያ ሲሆን ሰውነታችን ለበሽታው ከተጋለጠ በኋላ በሚኖሩ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በበሽታ ተከላካይ ህዋሳቱን ያመርታል።

ይህንን ተፈጥሯዊ የበሽታ መከላከያ አቅም ምርመራን ውጤት በማወቅ ብቻ ሕክምና መስጠት እንደማይቻል የጠቀሰው ተቋሙ፣ ነገር ግን በቀጣይ ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ እንደሚያገልግል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ የሚገኘው በሽታን የመከላከል ህዋስ (አንቲቦዲ) የመመረት ሁኔታ በእድሜ፣ በአመጋገብ፣ በሚጠቀማቸው መድኃኒቶች፣ በሚያጋጥመው በሽታ ከባድነት እና ባሉበት ተጓዳኝ በሽታዎች ላይ ይወሰናል ብሏል።