"በታቃውሞው የተገደለውን የልብ ጓደኛዬን ፍትህን በመሻት ነው ሰልፍ የወጣሁት"

"ጓደኛዬ ልቡ ሰፊ ነበር፤ ሁሉን መውደድ የሚችል" ትላለች ዳይመንድ

በኔብራስካ፣ ኦማሃ ነዋሪነቷን ያደረገችው ዳይመንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበራትን ስራ ስታጣ ከጎኗ የነበረውም ጓደኛዋ ጄምስ ስከርሎክ ነበር።

እሱም ሆነ ቤተሰቦቹ ወደ ቤታቸው ጋበዟት፤ የሚበሉትን በልተው፤ ቤት ያፈራውንም እንደቀማምሱም የቤተሰባችን አካል ነሽ አሏት። በህይወቷ ትልቅ ውለታ ውሎልኛል የምትለው ጄምስ ቤት አልባ ከመሆን አዳናት።

"መኖሪያ አጥቼ እሱም ሆነ ቤተሰቦቹ አለንልሽ ሲሉኝ፤ ከጓደኛዬ በላይ መሆኑን ተረዳሁኝ" በማለት ለሬዲዮ ዋን ኒውስ ቢት የተናገረችው ዳይመንድ "ወንድሜ ነበር" ብላለች።

ዳይመንድና የ22 አመቱ ጄምስ ጎረቤቶች ነበሩ።

የተገናኙትም በጋራ መኖሪያ ቤቶቻቸው (አፓርትመንታቸው) ግቢ ውስጥ በሚገኘው የመዋኛ ገንዳ ከሁለት አመታት በፊት ነበር።

ጄምስ ስራ ቦታ ይሸኛታል፤ የትምህርት ቤት ስራዎቿንም ያግዛታል። እስካሁንም ቢሆን ደብተሮቿ ላይ የሳላቸው ስዕሎች አሉ።

በሚወዱት ጓደኞቹ ጁጁ የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው ሲሆን በታናናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ የሚወደድ፤ ከሁሉ ጋር የሚቀልድ እንደነበርም ዳይመንድ ትናገራለች።

በግንባታ ሰራተኝነት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረ ሲሆን የሰባት ወር ልጁንም ለመንከባከብና አትኩሮትም ለመስጠት በሚል ስራውን አቆመ። በአባትነቱም ይኮራ ነበር ትላለች ዳይመንድ

የህፃን ልጁን የወደፊት ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውም ሁኔታ ስለሚያስጨንቀውም ነበር ጄምስ ለማህበራዊ ፍትህ መታገልን የመረጠው።

በተለይም በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ የተነሱ የ'ብላክ ላይቭስ ማተር' ተቃውሞዎች ላይም በከፍተኛ ሁኔታ ድምፃቸውን ካሰሙት መካከል አንዱ ነው።

ነገር ግን ግንቦት 22፣ 2012 ዓ.ም ጄምስ እንደወጣ አልተመለሰም።

የአንድ መጠጥ ቤት ባለቤት የሆነው ነጩ ጃኮብ ጋርድነር በሽጉጥ ተኩሶ እንደገደለውም የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ።

ጃኮብ ጋርድነር መጠጥ ቤቱ በር ላይ እየጠበቀ የነበረ ሲሆን፣ ጄምስ ከኋላው መጥቶ ሲይዘውም ሁለት ጊዜ በአየር ላይ ተኩሶ በማስከተል ጄምስን እንደመታው ታውቋል። ጄምስም በደረሰበት ጉዳት ህይወቱ አልፏል።

የግዛቱ አቃቤ ህግ የመጠጥ ባለቤቱ ራሱን ለመከላከል በሚል ነው የተኮሰው ስለዚህ ክስ አልመሰርትበትም ብሏል። ነገር ግን የአይን እማኞች ጃኮብ ጋርድነርና አባቱ ተቃዋሚዎችን የዘረኛ ስድብ ሲሳደቡ እንደነበርና ሲያስፈራሩም በማየቱ ጄምስ ለመከላከል ነው ከኋላ የገባው ብለዋል።

የህዝቡንም ቁጣ ተከትሎ አቃቤ ህጉ ከማህበረሰቡ የተውጣጣ ኮሚቴ ያዋቀረ ሲሆን ግለሰቡ ይከሰስ አይከሰስ በሚለውም ጉዳይ ላይ የሚወስኑ ይሆናል። የመጠጥ ቤቱ ባለቤት ጥፋተኛ ሆኖ ካገኙትም በግድያ ወንጀል እንዲሁም ፈቃዱ ያለፈበት የጦር መሳሪያ በመያዝ ክስ ይመሰረትበታል።

"ለውጥ መምጣት አለበት"

የኔብራስካዋ ኦማሃ የባለፈው ዓመት የህዝብ ቁጥር እንደሚያሳየው 77 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ ነጭ ነው።

የጄምስ መሞትንም ተከትሎ የኔብራስካ አስተዳዳሪ ፒት ሪኬትስ ጥቁሩን ማህበረሰብ ባናገሩበትም ወቅትም ስሜት አልባ ንግግር ነው በሚል ብዙዎች አቋርጠው ወጥተዋል።

ጓደኛዋ ሲሞት ዳይመንድ በቦታው አልነበረችም፤ ከዚያ በፊትም በነበሩት የተቃውሞ ሰልፎችም እንዲሁ አልተሳተፈችም።

የፖሊስ ጭካኔን ብትረዳም ፖለቲካዊ ተሳትፎዋ ግን የቀዘቀዘ ነበር።

ይህ ሁሉ ግን ጄምስ ሲሞት ተቀየረ። " ጄምስን እንደ ወንድሜ ነው የምወደው። እሱን ማጣት ማለት ተሰምቶኝ የማያውቅ ኃዘንና ህመም እንዲሰማኝ ሆኗል" በማለትም ተናግራለች።

የቅርብ ጓደኛዋንም ሞት ተከትሎ የኮሮናቫይረስ መመሪያዎች ሳያስጨንቋት ከጓደኞቿ ጋር ተቃውሞውን ተቀላቀለች። "መንግሥት በራሱ ህዝብ ላይ ተነስቷል" የምትለው ዳይመንድ "ህዝቡ ግን ከተባበረ በመንግሥትም ላይ ቢሆን ለውጥ ማምጣት እንችላለን" ትላለች።

"ተቃውሞዬን እቀጥላለሁ፤ ምርጡ ጓደኛዬ አሁንም ቢሆን ፍትህ አላገኘም" በማለትም ለኒውስ ቢት አስረድታለች።

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ከተገደሉት አስራ ዘጠኝ ሰዎች መካክለ ጄምስ አንዱ ነው።

አብዛኛዎቹ እንደ ጄምስ ምንም መሳሪያ ያልያዙ ጥቁር ወጣቶች ናቸው። አንዳንዶቹ በተተኮሰባቸው ጥይት ሲሞቱ፣ አንደኛው ደግሞ ሰልፈኞቹን የሚቃወም ግለሰብ በተሰበሰው ህዝብ መካከል መኪናውን በመንዳቱ ህይወቱ አልፏል።

ዳይመንድ ሌሎች ወጣቶች የብላክ ላይቭስ ማተር እንቅስቃሴን እንዲቀላቀሉና ተቃውሞቹም ሰላማዊ እንዲሆኑ ጥሪዋን አቅርባለች።

"ሁኔታው የከፋ ቢሆንም፤ ቤታችንን ማፍረስ የለብንም። ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሟችንን እያሰማን ደህንነታችንን እንጠብቅ" በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ዳይመንድ ቢቢሲን ባናገረችበት ወቅት ከጄምስ ቤተሰብ ጋር በመሆን ህይወቱን ለመዘከር የሚደረገውን የሃዘን ስርአት ለመካፈል እየተዘጋጀች ነበር።

ጄምስን የገደለው ወደ ፍርድ እንደሚቀርብ ተስፋን የሰነቀችው ዳይመንድ አጠቃላይ ለተገደሉትም "ፍትህን እንሻለን" ትላለች።

ጄምስ የወደፊቱን ብሩህ ነበር ብሎ ነበር የሚያስበው፤ ልክ እንደ ወንድሙ የንቅሳት አርቲስት እንዲሁም ኮሌጅ ገብቶም የማጥናት እቅድ ነበረው። ልጁም ሕይወቱ ነበረች ትላለች።

ሞቱንም ተከትሎ ብዙዎች በትዊተር ህይወቱን የዘከሩት ሲሆን ለመታሰቢያነቱም እንዲውል ትልቅ ቅርፅ ቆሞለታል።

"ሲሞት ታላቅ ስራ ሰርቶ እንደሚሞት ይነግረኝ ነበር" የምትለው ዳይመንድ

ጄምስ በሕይወት እያለም የራፕ ሙዚቃም ይጫወት፤ ለልጁ አርዓያ መሆንም ይፈልግ ነበር።

በስተመጨረሻም "ለትልቅ አላማ ነው የሞተው፤ ስሙም ከመቃብር በላይ ነው" ብላለች።