ኮሮናቫይረስ፡ በቀን ቢያንስ አስር ጊዜ እጅችንን መታጠብ

እጅ የሚታጠብ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀን ውስጥ ቢያንስ 10 ጊዜ እጅን በሳሙና መታጠብ እንደ ኮሮናቫይረስ አይነት ተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎች ጠቁመዋል።

መረጃው በአውሮፓውያኑ ከ 2006 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ተመሳሳይ አወቃቀር ባላቸው ቫይረሶች ዙሪያ በተደረገ ጥናት የተገኘ ነው።

ኮሮናቫይረስ ቀለል ያለ የጉንፋን አይነት ህመም ከሚያስከትሉ ቫይረሶች ነው የሚመደበው።

ታዲያ እነዚህን የቫይረስ አይነቶች፣ ኮሮናቫይረስን ጨምሮ ማለት ነው፣ በቀላሉ በውሀ እና በሳሙና በመታጠብ ብቻ ልንገድላቸው እንችላለን።

የእንግሊዙ የህክምና ጥናት ካውንስል በየዓመቱ በጋ ሲገባ ሰዎች ጉንፋን መሰል የመተንፈሻ አካላትን በሚያጠቃ ቫይረስ መያዛቸውንና የበሽታውን ምልክቶች ማሳየታቸውን ያጣራል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ቀላል ጉንፋን የያዛቸውን ሰዎች በኮሮረናቫይረስ ከተያዙት ለመለየት አስችሎታል።

ጥናቱ ሲደረግ ለመሳተፍ ፈቃደኛ በነበሩ 1663 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ቢያንስ በቀን ስድስት ጊዜ እጃቸውን በውሃ እና በሳሙና የሚታጠቡ ሰዎች በእንደዚህ አይነት ቫይረሶች የመያዝ እድላቸው በእጅጉ ዝቅተኛ ነው።

ነገር ግን ይላሉ ተመራማሪዎቹ፤ እጃችንን በቀን አስር ጊዜ መታጠባችን ብቻ ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቀን አይችልም። ምክንያቱም ቫይረሱ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን ንክኪና ትንፋሽ አማካይነት መተላለፍ ይችላል።

የጥናቱ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ሳራ ቢል እንደሚሉት ማንኛውም አይነት የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን አሳየንም አላሳየንም እጃችንን በቀን ውስጥ ደጋግመን መታጠብ እንደ ባህል ሊሆን ይገባል።

‘’ እጃችንን መታጠባችን እራሳችንን ከቫይረስ ከመከላከል ባለፈ በዙሪኣችን ወዳሉ ሰዎች የማስተላለፍ እድላችንን ይቀንሰዋል።‘’

የእንግሊዝ ማህበረሰብ ጤና ቢሮ ደግሞ እጃችንን በውሃ እና በሳሙና ቢያንስ ለ20 ሰከንድ ያክል መታጠብ የኮሮናቫይረስ ስርችትን ከምናስበው በላይ ለመቆጣጠር ይረዳል ይላል።

በተለይ ደግሞ ካስነጠስን፣ ካሳልን ወይም አፍንጫችንን ከጠራረግን በኋላ እጃችንን በፍጥነት መታጠብ በጣም ጠቃሚ ነው።

ከቤታችን ወጥተን የነበረ ከሆነም ልክ ስንመለስ በአግባቡ እጃችንና ፊታችንን በሳሙና መታጠብ ያስፈልጋል።

ኮሮና
Banner