ኮሮናቫይረስ፡ ከቤት መውጣት ሊያስጨንቀን ይገባል?

አንዳንድ አገራት የእንቅስቃሴ ገደብ እያላሉ ነው። የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በበኩላቸው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ ሕይወት ምን ሊመስል ይችላል? የሚለው በርካቶችን እያስጨነቀ ነው ይላሉ።

የ25 ዓመቷ ጸሐፊና የአዕምሮ ጤና እንዲሁም የሴቶች መብት ተሟጋች አካንክሻ ባሂታ፤ “ለብዙዎቻችን ሕይወት ምቹ አይሆንም” ትላለች።

የእንቅስቃሴ ገደቡ ከመጣሉ በፊትም ጭንቀት ውስጥ የነበረችው ጸሐፊ፤ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ተገልለው ሲኖሩ ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚያድርባቸው በማኅበራዊ ሚዲያ ትገልጻለች፤ ከተከታዮቿ ጋርም ትወያያለች።

ደልሂ ትኖር የነበረው አካንክሻ፤ ሕንድ እንቅስቃሴ ስትገታ ወደ ቼናይ አቅንታ ከቤተሰቦቿ ጋር ተቀላቅላለች። የአንድ ወር ቆይታዋ ቀላል አልነበረም። በጣም የከፋት ቀን ታለቅሳለች። አብዛኛውን ጊዜ በግሏ መሆንን ትመርጣለች።

“ይህም ያልፋል እያሉ ለራስ መንገር ብቻ ነው የሚቻለው” ትላለች።

“ጭንቀት ላለበት ሰው ከቤት መውጣት በራሱ ስቃይ ነው”

ማኅበራዊ መስተጋብሮች የሚያስጨንቋት ጸሐፊቷ፤ የቤተሰቦቿ ድጋፍ አልተለያትም። ከቤተቦቿ ጋር መሆን ያስደስታታል። የእንቅስቃሴ ገደብ ሲነሳ እንዴት ወደቀደመ ሕይወቷ እንደምትመለስ ስታስብ ግን ትጨነቃለች።

“ጭንቀት ላለበት ሰው ከቤት መውጣት በራሱ ስቃይ ነው” ትላለች። ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ከተለመደ በኋላ ዳግመኛ ወደ ውጪ መውጣት አስፈሪ መሆኑን ታስረዳለች።

ከህክምና ባለሙያዎች እስከ ነጋዴዎች ድረስ በርካቶች ጭንቅ ውስጥ ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥ የብዙዎቻችን ሕይወት እንዳልነበረ መሆኑም እሙን ነው።

ካናዳ ውስጥ የሚሠሩት የሥነ ልቦና ምሁር ዶ/ር ስቲቨን ቴይለር፤ “ሰዎች እንቅስቃሴ አልባ ሕይወትን ለመላመድ እየሞከሩ ነው” ይላሉ።

ይህን ሕይወት መላመድ እንቅስቃሴ ሲጀመር ውዝግብ ውስጥ ሊከት ይችላል።

“ሰዎች እንቅስቃሴ መቆሙን ተላምደው፣ ከወደዱት ከቤት መውጣት ሊያጨንቃቸው ይችላል” ይላሉ ዶ/ር ስቲቨን።

ዓለም ስለ ኮሮናቫይረስ ከመስማቱ ከሳምንታት በፊት ስለ ወረርሽኝ እና ሥነ ልቦና መጽሐፍ ያሳተሙት ባለሙያው፤ የቫይረስ ሥርጭት እንዲሁም በቁጥጥር ሥር የመዋሉ ነገር ከሥነ ልቦና ጋር ይተሳሰራል ይላሉ።

ዜጎችን ለድሕረ ወረርሽኝ ሕይወት ማዘጋጀት

አገራት እንቅስቃሴ ላይ የጣሉትን ገደብ ሲያላሉ ዜጎች ደህንነት እንዲሰማቸው መደረግ እንዳለበት ዶ/ር ስቲቨን ያስረዳሉ።

“ዜጎች ለድሕረ ወረርሽኝ ሕይወት እንዲዘጋጁ መደረግ አለበት። አሁን ከሰዎች ጋር መተቃቀፍ፣ ሬስቶራንት ሄዶ መመገብ ይቻላል መባል አለበት” ይላሉ።

ሰዎች በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ስጋት ውስጥ እንዳይወድቁ መመሪያ መሰጠት አለበት። አንዳንዶች ከቤት የመውጣት ፍርሀት እያደረባቸው እንደሆነም ባለሙያው ይናገራሉ።

“በበሽታው እያዝ ይሆን ብለው ይፈራሉ፤ ሆኖም ግን በሳምታት ወይም በወራት እድሜ ይህ ጭንቀት ይወገዳል።”

በሌላ በኩል ጭንቀቱ የረዥም ጊዜ የሥነ ልቦና ጠባሳ የሚጥልባቸውም አሉ። ለምሳሌ ጸሐፊቷ አካንክሻ፤ ሕንድ እንቅስቃሴ ላይ የጣለችውን ገደብ ስታነሳ ምን ዓይነት ሕይወት ይጠብቀኝ ይሆን? ብላ እየተጨነቀች ነው።

“ብዙዎች የእንቅስቃሴ ገደቡ የሚነሳበትን ቀን በጉጉት እየጠበቁ ነው፤ እነሱ ያሉበትን ስሜት ግን እኔ አልረዳም” ትላለች። የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚመክሩት፤ አመጋገቧን አስተክላለች። የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ትሠራለች።

“ሁሉም ነገር ቀለል አርገን መጀመር አለብን። በየቦታው ድግስ ተጥሎ አዕምሮዬን መሳት አልፈልግም” ስትልም ትናገራለች።

የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ ከሚኖረው ለውጥ ጋር ለመላመድም ራሷን እያዘጋጀች ነው።