ኮሮናቫይረስ፡ "ስለምንወዳችሁ ሠርጋችን ላይ አትምጡ" የአዲስ አበባዎቹ ሙሽሮች

ሙለታ ጉርሜሳ እና እመቤት ምስጋና እሁድ (በ18/8/2012) እለት ነው የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን የፈፀሙት።

ሠርጋቸውን አቅደው የነበረው ግንቦት ወር ላይ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽን መከሰትና በአጭር ጊዜ ውስጥም ከአገርም ሆነ ከዓለማችን ላይ ገለል ሊል እንደማይችል ስላመኑ ሃሳባቸውን ቀየሩ።

ስለዚህ የጋብቻ ቀናቸውን ካሰቡት ጊዜ አሳጠሩት።

እዚህ ላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትዝ አላቸው። ለአምስት ወራት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአራት በላይ ሆኖ መሰብሰብ እና ሠርግም ሆነ ሌላ ድግስ ተከልክሏል።

ታዲያ እንዴት አድርጎ ሠርግን በአራት ሰው ብቻ ማካሄድ ይቻላል? የጥንዶቹ እናት አባት ብቻ አራት ይሆናሉ። የቅርብ ቤተሰብ፣ ቃልኪዳን የሚያስፈፅም የኃይማኖት አባት፣ የካሜራ ባለሙያ እነዚህ እንኳን ቢቆጠሩ ከአስር በላይ ናቸው።

በዚህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ወቅት ለመጋባት የሚወስኑ ከሆነ ኮስተር ያለ ውሳኔ ይጠብቃቸዋል።

ሠርጋቸውን የመንግሥት ሕግ ሳይጥሱ ለማድረግ እንዲችሉ አራት ሰው ብቻ በመሆን እንዴት መጋባት እንደሚችሉ አሰቡ።

ሙሽሪትና ሙሽራው፣ በተጨማሪም በሁለቱ ወገኖች አንድ አንድ ሰው ቢሆን አራት ሰው ብቻ የታደመበት ሠርግ ይሆናል በሚል ወሰኑ። ካህኑስ?

አምስት ቢሆን አደጋውን መቀነስ ይቻላል፤ ስለዚህ ሙሽራውንና ሙሽሪትን ጨምሮ አምስት ሰው የታደመበት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ለማድረግ በአንድ ድምጽ ወሰኑ!

የሚዜ ጋጋታ፣ የቤተሰብ እልልታ እንዲሁም የወዳጅ ዘመድ ግርግር ያልታየበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያልጣሰ፣ የኮሮናቫይረስ መከላከል ትምህርቶችን ተግባራዊ ያደረገ ሠርግ አካሄዱ።

ሠርጉ አዲስ አበባ ውስጥ ጀሞ ቤተል መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው የተፈፀመው። ጥንዶቹ ከዚህ ቀደም ያይዋቸውንና የተካፈሉባቸውን ሠርጎች ያስታውሳሉ።

የቤተክርስቲያኒቷ አዳራሽ ሞልቶ፣ ሠርገኛውና እድምተኛው ተገፋፍቶ፣ እጅ እስኪቃጠል እያጨበጨቡ፣ እልልታውና ሽብሸባው የበዛበት ነበር።

የእነርሱ ሰርግ ግን ጭር ያለ ነው- አራት ሰው ብቻ የታደመበት። ከቄሱ ጭምር አምስት ሰው ብቻ።

ለዘመዶች፣ ቤተሰቦች እንዲሁም ጓደኞች መልዕከት አስተላልፈዋል። ልንጋባ ነውና ኑ አይልም የጥሪ መልዕክቱ። "ስለምንወዳችሁ ሠርጋችን ላይ አትገኙ" የሚል እንጂ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሲያልፍ "ነገም እኛ የእናንተው ነን" ዛሬ መሰብሰባችን ጉዳት አለው። ባላችሁበት ሆናችሁ ደስታችንን ተካፈሉ ማለታቸውን ይናገራሉ ሙለታና እመቤት።

ጥንዶቹ ወላጆቻቸው የልጆቻቸውን ሠርግ ለመታደም ጓጉተው እንደነበር ገልጸዋል። ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት በትንሹ ሰባ ሰው ቢበዛ ደግሞ መቶ ሰው ጠርተው ለመሰረግ አቅደው ነበር። ይህ ሳይሆን ሲቀር ቤተሰቦቻቸውን ይቅርታ መጠየቃቸውን ሙለታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከሠርግ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤታቸው ገብተው መቀመጣቸውን ገልፀዋል። የሠርግ ልብሳቸውን ቤተክርስቲያኑ ውስጥ አውልቀው መሄዳቸውን አክለዋል።

በቃ ጠያቂም ተጋባዥም ጋባዥም የለም። ይህ ሁሉ እስኪያልፍ ባልና ሚስት በአንድ ጎጆ በፍቅር ካባ ተጀቡነው ተቀምጠዋል።

መልካም የትዳር ዘመን!