በህዋ ላይ ፊልም ለመቅረጽ ቶም ክሩዝ እና ናሳ ተጣመሩ

እውቁ ተዋናይ ቶም ክሩዝ እና ናሳ በህዋ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊልም ለመቅረጽ ተጣመሩ።

የፊልሙ ይዘት ባይታወቅም፤ ቶም ክሩዝ ከሚሰራው ተከታታይ ፊልም 'ሚሽን፡ ኢምፖስብል' ጋር አይገናኝም ተብሏል።

የናሳ አስተዳዳሪ ጂም ብራይደንስታይን በትዊተር ገጻቸው ላይ ናሳ ከቶም ክሩዝ ጋር በህዋ ላይ የፊልም ቀረጻ ሊያካሂድ መሆኑ እንዳስደሰተው ገልጸዋል።

ቶም ክሩዝ እአአ 2013 በወጣው 'ኦብሊቪዮን' ፊልም ላይ የምድርን ተፈጥሯዊ ሃብት ከእንግዳ ወራሪ አካላት ሲታደግ ተውኗል።

በድርጊት በተሞሉ ፊልሞቹ ላይ አደገኛ የሚባሉ ትዕይንቶችን እራሱ በመተወን የሚታወቀው ቶም ክሩዝ ሁልግዜም ቢሆን ፈታኝ የሆኑ የፊልም ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ይታወቃል።

ከቶም ክሩዝ ጋር 'ቶፕ ጋን' የተሰኘ ፊልም አብሮ የተወነው ማይልስ ቴለር "አንድን ሥራ መከወን አይቻልም ሲባል ነው ቶም ወደ ሥራ የሚገባው" ብሏል።

ቶም ክሩዝ በድርጊት የተሞሉ ፊልሞችን ሲሰራ ብዙ ጉዳቶች ደርሰውበታል።

እአአ 2017 ላይ የሚሽን ኢምፖስብል ተከታይ የሆነውን ፊልም ሲሰራ ከጣሪያ ላይ ሲዘል ቁርጭምጭሚቱ ተሰብሮ ነበር።

ቶም ክሩዝ ስለዚህ አጋጣሚ 'ዘ ግራሃም ኖርተን ሾው' ለተባለ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲናገር፤ "እንደተሰበረ አውቄ ነበር። 'እህ' ብቻ ብዬ ካሜራውን አለፍኩ። ያ ትዕይንት የፊልሙ አካል ሆኗል" ብሏል።

2011 በወጣው 'ሚሽን፡ ኢምፖስብል-ጎስት ፕሮቶኮል' ፊልም ላይ፤ ሚስተር ሃንትን ሆኖ የሚተውነው ክሩዝ የዓለማችን ረዥም ህንጻዎች መካከል አንዱ የሆነውን የዱባዩን ቡርጀ ከሊፋ ህንጻ በገምድ ታስሮ ሲወጣ ታይቷል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ቶም ክሩዝ ለመብረር እየተንደረደረ ያለ አውሮፕላን የውጪ ክፍል በጣቶቹ ይዞ ሲንጠለጠል ታይቷል።