ዕጩው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የወሲብ ትንኮሳ ክስ ቀረበባቸው

ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉት ጆ ባይደን ከ30 ዓመታት በፊት የምክር ቤት አባል ሳሉ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ አስተባበሉ።

የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሰውብኛል ስትል ክስ ያቀረበቸው ሴት ታራ ራይድ ትባላለች። ከዓመታት በፊት በባይደን ቢሮ ውስጥ ረዳት ሆና ለአጭር ጊዜ ሠርታ ነበር።

"የቀድሞው አለቃዬ ጆ ባይደን ወደ ግድግዳው ወስዶ ካስደገፈኝ በኋላ እጁን በቀሚስ ውስጥ ሰደደ…" ትላለች ትንኮሳው እንዴት እንደደረሰባት ስታብራራ።

የባይደን የምረጡኝ ዘመቻ አስተባባሪ በበኩሏ ይህ በፍጹም አልተደረገም፤ ነጭ ውሸት ነው ስትል አስተባብላለች።

"ጆ ባይደን ሴቶች መደመጥ አለባቸው ብሎ የሚያምን፤ ሴት ልጅን የሚያከብር ሰው ነው። ነጻ ሚዲያው እንዲህ አይነት ክሶችን በጥንቃቄ ነው መዘገብ ያለበት" ብላለች የባይደን የምረጡኝ ዘመቻው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ።

የቀድመው ሴናተር፣ በኋላም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆ ባይደን በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ይቀናቀናሉ ተብለው እየተጠበቁ ነው። ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የመሆን ዕድላቸውም ጠባብ የሚባል አይደለም።

በተለይ የቀድሞ አለቃቸው ባራክ ኦባማ ጆ ባይደንን ይሁንታ ሰጥተው ስለባረኳቸው ሰፊ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።

ከሳሻቸው ታራ ራይድ ይህ ድርጊት ተፈጽሞብኛል የምትለው ከ30 ዓመት በፊት ጆ ባይደን ሴናተር ሳሉ ነው። ወሲባዊ ትንኮሳው እንዴት እንደተፈጠረ ስታስታውስም፤

"ማንም አልነበረም። የስፖርት ትጥቅ የያዘ ቦርሳ ለባይደን አድርሺ ተባልኩ፤ ቢሮ ውስጥ ብቻችንን ነበርን፤ ምንም ትንፍሽ ሳይል ወደ ግድግዳው ከገፋኝ በኋላ እጁን ወደ ቀሚሴ ሰደደ…"

"…በዚህ ጊዜ ባይደን ስገፈትረው 'ሌላ ቦታ መሄድ ትፈልጊያለሽ?' አለኝ፤ ከእቅፉ መንጭቄው ስወጣ ደግሞ፣ 'ተይ እንጂ አንቺ ልጅ…እንደምትወጂኝ እኮ ሰምቻለሁ" አለኝ ስትል በፖድካስት ቃለ ምልልስ ላደረገችላት ጋዜጠኛ አብራርታለች።

"እንደምትወጂኝ እኮ ሰምቻለሁ…" ያለኝ ነገር ዛሬም ድረስ ስሜቴን ያውከዋል ብላለች።

ታራ አሁን 56 ዓመቷ ነው።

ከሁሉም በላይ ጆ ባይደን የሴት መብት ተቆርቋሪ ሆኖ ለመታየት መሞከሩ ያንገበግበኛል ብላለች።

ጆ ባይደን ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ምክትላቸው የሚያደርጓት ሴት እንደሆነች ቃል ገብተው ከወዲሁ ምልመላ ጀምረዋል።

ወ/ት ታራ ከቀናት በፊትም በወሲብ ትንኮሳ የክስ መዝገብ ያስከፈተች ሲሆን ተንኳሿን ግን ማን እንደሆነ ለጊዜው አልጠቀሰችም።

እንደ ወ/ት ታራ ዓይነት ጆ ባይደን ትንኮሳ አደረሰብን ያሉ ሌሎች 7 ሴቶች ወደ ሚዲያ የቀረቡ ሲሆን አንዳቸውም መደበኛ ክስ አልመሰረቱም።

ራሳቸውም እንዳመኑት ጆ ባይደን ሴቶችን የማቀፍ፣ ጸጉራችንና ጀርባቸውን የመነካካት ልምድ ነበራቸው። "ያን ልማድ እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ፤ ዕድሜ "ሚቱ" ለተሰኘው ጸረ-ጾታዊ ትንኮሳ ዘመቻ" ብለዋል።

ይህ በብዙ አሜሪካዊያን ዘንድ ሰውየው እስከዛሬ ለፈጸሙት ትንኮሳ እንደ ይቅርታ ቃል ተወስዶላቸዋል።

የቢቢሲዋ ካቲ ኬይ እንደጻፈችው ይህ በጆ ባይደን ላይ የቀረበው የጾታ ትንኮሳ ክስ በብዙ ምክንያቶች "ብዙ ርቀት አይሄድም።"

ምክንያቱ ደግሞ ከሳሿ ከዚህ ቀደም በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ቀርባ አሁን ከገለጸችው ለየት ያለ ታሪክ መናዘዟ ነው።

በተጨማሪም እንዲህ ዓይነት ክሶች መሠረት እንዲኖራቸው ተከሳሹ እንዲህ አይነት ድርጊት የሚፈጽም መሆኑን የሚያስረዳ ተደጋጋሚ ክሶች ሊኖሩ ይገባል። ከሳሾችም ያልተዛባ ምስክርነት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

የወ/ት ታራ ክስ እምብዛምም ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚያሳየው ትላለች የቢቢሲዋ ካቲ "ሚዲያዎች በሚገባው መጠን እያጦዙት አለመሆኑ ነው።"

ምናልባት የሴትዮዋን የጾታ ትንኮሳ ክስ ዶናልድ ትረምፕ ጆ ባይደንን ለማጠልሸት ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ በትንሹ 24 ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ እንዳደረሱባቸው በመግለጽ ወደ ሚዲያ ወጥተው እንደነበር ይታወሳል።