ኮሮናቫይረስ፡ ዴንማርክ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የዘጋችውን በሯን ለመክፈት ለምን ቸኮለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴንማርክ የእንቅስቀሴ እቀባዋን ለማላላት ተፍ ተፍ እያለች ነው። ከነገ ረቡዕ ጀምሮ 11 ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ አዳጊዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ይችላሉ።
ይህን ለማድረግ ከአውሮፓ አገሮች ቀዳሚዋ ናት።
ዴንማርክ ከወራት በፊት ወረርሽኙ ሲጀማምር ሰሞን ትምህርት ቤቶችንም ሆነ የንግድ ተቋማትን ለመዝጋት ከቀዳሚ አገራት ተርታ ነበረች።
"ከሚያስፈልገን ጊዜ በላይ በራችንን መዝጋት ያለብን አይመስለንም" ብለዋል ክብርት ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬድሪክሰን።
ከሞላ ጎደል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዴንማርክ በቁጥጥር ሥር የዋለ ይመስላል። መንግሥት የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት እንደገና ማንቀሳቀስ ይፈልጋል።
ዴንማርክ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ግን ግብታዊ የሚባል አይደለም። በከፍተኛ ጥንቃቄ እየሆነ ያለ ነው። ንግዶችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች እየተከፈቱ የሚመጡትም ቀስ በቀስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ፍሪድሪክሰን እንዳሉት ነገሩ በቀጭን ገመድ ሚዛንን ጠብቆ እንደመራመድ ያለ ነው።
"ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ከከፈትነው፣ ወረርሽኙ በአንድ ጊዜ ሰማይ ይነካል፤ ያን ጊዜ በድጋሚ ለመዝጋት እንገደዳለን" ብለዋል።
ሆኖም ዴንማርክ ድንበሮቿ ዝግ እንደሆኑ ይቆያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከዴንማርክ ሌላ የትኞቹ አገራት በራቸውን እየከፈቱ ነው?
ኖርዌይና ኦስትሪያም የዴንማርክን ፈለግ እየተከተሉ ነው። ቀስ በቀስ በራቸውን በትንሹ መክፈት ይዘዋል።
ኦስትሪያ እንዲያውም ዛሬ ማክሰኞ ሱቆችን ከፋፍታለች። ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም ቀስ በቀስ እየተከፈቱ ነው።
ኖርዌይ ከ6 ቀናት በኋላ በኤፕሪል 20፣ የመዋዕለ ሕጻናትና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ትፈቅዳለች።
ቡልጋሪያ የገበሬዎች እርሻ እንዲከፈት ፈቅዳለች። በቼክ ሪፐብሊክ ደግሞ መናፈሻዎች ተከፍተዋል። የሕንጻ መሣሪያ መደብሮች ወደ ሥራ ተመልሰዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ የተመሰቃቀለችው ስፔንም ከሰኞ ጀምሮ አንዳንድ እንቅስቃሴዎቿ ወደነበሩበት ይመለሳሉ ተብሏል። ዜጎች የአፍ-አፍንጫ ጭምብል በየአውቶቡስ ተራና ባቡር ጣቢያ ይታደላቸዋል ተብሏል።
ከነዚህ የአውሮፓ አገራት ውጭ ያሉት ግን ከወረርሽኙ በፊት የነበረውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደነበረበት ለመመለስ ጊዜው ገና ነው ብለው ያምናሉ።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ "እንዲህ ዓይነቱን ነገር ለማሰብ የምንሞክርበት ወቅት ላይ አይደለንም" ብለዋል።
ዴንማርክ ለምን ቸኮለች ታዲያ?
ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ጋር ሲነጻጸር ዴንማርክ እግዱን በመጣሉም ሆነ በማንሳቱ ቀዳሚ ናት ብለናል። ለምሳሌ የመጀመርያውን እግድ የጣለችው ከዩናይትድ ኪንግደም በሁለት ሳምንት ቀድማ በማርች 11 አካባቢ ነበር።
ያን ጊዜ ዴንማርክ ከ10 ሰው በላይ በአንድ ቦታ እንዳይሰባሰብ፣ ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዳይሄዱ፣ ድንበሮችም እንዲዘጉ ነበር የወሰነችው።
ይህ ግን ከጎረቤቷ ስዊድን ፍጹም የተለየ ውሳኔ ነበር።
በስዊድን ብዙዎቹ ነገሮች ከወረርሽኙ በፊት እንደነበሩ ነው ያሉት ማለት ይቻላል። በቅርቡ ብቻ ከ500 ሰዎች በላይ መሰብሰብ የሚከለክለውን ደንብ ወደ 50 ዝቅ አድርጋለች።
ነገር ግን የዴንማርክን የወረርሽኝ ጊዜ ደንብ ከነፈረንሳይና ጣሊያን እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም ጋር ካስተያየነው እጅግ የላላ ሆኖ እናገኘዋለን።
ለምሳሌ ዴንማርክ ቤት ውስጥ ቆልፋችሁ ዋሉ የሚል ደንብ አልነበራትም። ቡና ቤቶች፣ ስፖርት ቤቶችና ጸጉር ቤቶች ዝግ እንዲሆኑ ብታዝም አነስተኛ ሱቆች ዝግ እንዲሆኑ ግን አልደነገገችም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጤና ስታትስቲክስ ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ዴንማርክ ከብዙ የአውሮፓ አገሮች በአንጻራዊነት ልል የነበሩ ድንጋጌዎቿ ጎድቷታል ብሎ መደምደም ይከብዳል።
እስከ ሰሞኑ ድረስ ዴንማርክ የሞቱባት 260 ሰዎች ብቻ ናቸው። ተያዙ የተባሉት ሰዎች ቁጥርም 6 ሺህ አካባቢ ነው።
ይህ ከነጣሊያንና ስፔን እንዲሁም ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል ቁጥር አይደለም። ምንም እንኳ አንድ ሞትም ቢሆን ሕይወት ስለሆነ የሚያስቆጭ ቢሆንም።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ልዩ የሚያደርጋት በዴንማርክ ወደ ጽኑ ሕሙማን የሚገቡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፤ ከዚህ ወር መግቢያ ጀምሮ።
ዴንማርክ በዚህ ሰዓት የመደበኛ ታማሚ አልጋ፣ የጽኑ ሕሙማን አልጋዎችና የሕክምና መሣሪያዎች በሽበሽ ናቸው።
አሁን ዴንማርክ እየተዘጋጀች ያለችው ድንገት ወረርሽኙ ቢያገረሽ በአንድ ጊዜ በርካታ ዜጎችን ለመመርመር የሚያስችል አቅም መፍጠር ላይ ነው።
በዚህ ጊዜ በር መክፈት፣ እቀባን ማንሳት ያዋጣል?
የዓለም ጤና ድርጅት አለቃ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም አገራት በራቸውን ለመክፈት የሚያሳዩት ጉጉት አሳስቧቸዋል። እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ነው ሲሉ ነው ያስቀመጡት፤ ትናንትና።
ዴንማርክ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤቶች ስትልክ ደንቦች ተፈጻሚ ይሆናሉ። ለምሳሌ ተማሪዎች ተጠጋግተው አይቀመጡም፤ ተጠጋግተው አይጫወቱም።
እንዲያውም ተማሪዎች ከክፍል ውስጥ ተቀምጠው ሳይሆን ደጅ ሆነው ነው በብዛት የሚማሩት።
በዴንማርክ አዳጊዎችን ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ ውሳኔ በሕዝብ ላይ ምን ስሜት አሳደረ ሲል ቢቢሲ ገምግሟል።
ለምሳሌ አንድ የፌስቡክ ማኅበር ተከፍቷል። "ልጄ የኮቪድ-19 መሞከሪያ አይጥ አይደለም" የሚል ነው የማኅበሩ ስም። በአጭር ጊዜ 35 ሺህ ሰዎች ወደውት አባል ሆነዋል።
ሌላ አንዲት የገበያ ጥናት ባለሞያ ስለ ውሳኔው ለቢቢሲ ስትናገር፣ "ሦስት ልጆች አሉኝ፤ ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ምንም ስጋት የለብኝም፤ እኔም ሥራዬን ከቤት ሆኜ ለማቀላጠፍ ይመቸኛል" ብላለች።
የዴንማርክ መንግሥት ልጆች ትምህርት እንዲጀምሩ ስለመወሰኑ ወላጆች ያላቸውን አስተያየት የሰበሰበ አንድ ተቋም 86 ከመቶ የሚሆኑት በውሳኔው ደስተኞች ናቸው ብሏል።














