ኮሮናቫይረስ፡ ጁሊያን አሳንጅ በድብቅ የወለዳቸው ሁለት ልጆች "ተገኙ"

የዊኪሊክስ መስራች ጂሊያን አሳንጅ በኢኳዶር ኤምባሲ ተጠልሎ ሳለ የወለዳቸው ሁለት ልጆች እንደነበሩ ይፋ ሆነ።

ይህን ምስጢር ይፋ ያደረገችው ደግሞ የልጆቹ እናት ስቴላ ሞሪስ ናት።

ይህን ነገር ለማንም ተናግሬው አላውቅም። አሁን በኮሮናቫይረስ ምክንያት አባታቸው በእስር ቤት እንዳይሞት ስለሰጋሁ ነው ምስጢሩን የዘረገፍኩት ብላለች ስቴላ።

እሷ እንደምትለው ከጁሊያን አሳንጅ ጋር በፈረንጆቹ 2015 ቀደም ብሎ እውቂያ ነበራቸው። ከ2015 ወዲህ ደግሞ ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተው ኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ያሳድጉ ነበር።

ጁሊያን አሳንጅ ጥብቅ የአሜሪካ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ምስጢሮችን አደባባይ አስጥቷል በሚል በአሜሪካ ይፈለጋል። በስለላ ወንጀልም ክስ ተደቅኖበታል።

ለዓመታት ስዊድንና አሜሪካ ተላልፎ ይሰጠን ቢሉም አሳንጅ ኢኳዶር ኤምባሲ ተጠልሎ ኖሯል።

ኢኳዶር የመንግሥት ለውጥ ማድረጓን ተከትሎ ለአሳንጅ የሰጠችውን ከለላ ስታነሳ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ እስር ቤት ተወስዷል።

አሁን በእንግሊዝ ቤልማሪሽ እስር ቤት ደህንነቱ ስላሰጋኝ ነው ይህን ለዓመታት ይዜው የቆየሁትን መረጃ ይፋ ለማድረግ የተገደድኩት ብላለች እጮኛው ስቴላ። ኮሮና ከያዘው አይድንም፤ ጤናው ተቃውሷል ስትል ይፋ አድርጋለች።

አሳንጅ ከተጠለለበት ኢኳዶር ኤምባሲ ተጎትቶ ከወጣ ወዲህ ቤልማሪሽ እስር ቤት ይገኛል። አሳንጅ የሚገኝበት ወህኒ ቤትን ጨምሮ በእንግሊዝ እስር ቤቶች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሆኗል።

አሜሪካ አሁንም ቢሆን አሳንጅ ጥብቅ የምላቸውን ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ምስጢሬን የዘረገፈ ስለሆነ ተላልፎ ይሰጠኝ ትላለች።

የ48 ዓመቱ አውስትራሊያ አሳንጅ በበኩሉ በጤናው መቃወስ ምክንያት የዋስ መብቱ እንዲከበር እየታገለ ነው።

የልጆቹ እናት ሞሪስ የደቡብ አፍሪካ ዜጋ ስትሆን አሳንጅን የሕግ ድጋፍ ከሚሰጡት የሕግ አዋቂዎች አንዷ ነበረች። እሱን ለጀመሪያ ጊዜ ያገኘችውም በፈረንጆች 2011 እንደነበር ትናግራለች።

የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት በተጠለለበት የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ከ2012 ጀምሮ ሲሆን ከዚያ በኋላ ሁለት ወንድ ልጆችንም አፍርተናል ብላለች።

ያን ጊዜ አሳንጅ ሴት ከመድፈር ጋር የተያያዘ ያልተዘጋ ክስ ስለነበረበት ስዊድን ተላልፎ እንዲሰጣት ጠይቃ ነበር። በኋላ ስዊድን ይህን ክስ ውድቅ እንዲሆን አድርጋለች። አሜሪካ በበኩሏ በስለላ ወንጀል ትፈልገዋለች።

ሞሪስ ይፋ እንዳደረገችው ከጁሊያን አሳንጅ ጋር በፍቅር የወደቀችው በ2015 በፈረንጆች ሲሆን ከ2 ዓመት በኋላ እዚያው ኤምባሲ ተጫጭተዋል።

የአሳንጅ ልጆች ሁለት ሲሆኑ ትልቁ ጋብሬል 3 ዓመቱ ሲሆን ትንሹ ማክስ የአንድ ዓመት ሕጻን ነው።

በዚያ በተጠለለበት ወቅት ቤተሰብ መመስረት የእስረኛነት ስሜት እንዳይሰማው አድርጎ ነበር ትላለች ስቴላ።

ብዙ ሰው ይህን ድርጊቱ እብደት አድርጎ ሊወስደው ቢችልም ለሱ ግን ከነበረበት ሁኔታ አንጻር ጤንነት ነበር ትላለች።

ነገሮች ሁሉ ለአሳንጅ ጨለማ በሆኑበት ወቅት ልጆቹ ተስፋ ብርሃን ሆነውታል፤ ደስተኛም ነበር ብላለች።

ጁሊያን አሳንጅ እጅግ ጥብቅ የሚባሉ በሺ የሚቆጠሩ የጽሑፍና የምስል ምስጢሮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን በተለይም የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ 18 ንጹሃንን የኢላማ ጨዋታ በሚመስል ሁኔታ እንደቀልድ ከሄሌኮፕተር ሆነው ሲገድሉ የሚያሳይ የቪዲዮ መረጃ በመላው ዓለም ቁጣን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።

አሳንጅ ለእንግሊዝ መንግሥት ባለፈው ዓመት ተላልፎ እስኪሰጥ ድረስ ለ7 ዓመታት በኢኳዶር ኤምባሲ ተጠልሎ ቆይቷል።