ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእንቅስቃሴ ላይ በተጣለው ገደብ ለችግር ለተጋለጡ የአማራ ክልል ድጋፍ እያደረገ ነው
የአማራ ክልል መንግሥት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት እንቅስቃሴዎችን ባገደባት ባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ችግረኞች የምግብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እገዳውን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎችን የማገዝ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
"በዕለታዊ ገቢ የሚኖሩትን ከሰኞ ጀምሮ ቤት ለቤት በመሄድ በነፍስ ወከፍ ስሌት የዱቄት እድላ እየተደረገ ነው። በተጨማሪም በከተማው ከንቲባ በኩል አቅርቦቱ እንደቀጠለ ነው" ብለዋል።
በተጨማሪም የጎዳና ተዳዳሪዎችንና በቤተ እምነት አካባቢዎች የሚገኙ ችግረኛ ሰዎች በመሰብሰብ መስተዳደሩ በመመገብ ላይ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
በእንቅስቃሴ እገዳው ወቅት ቀረው ነዋሪ የአቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው መግዛት ለሚችለው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሰፈር ለሰፈር የሽንኩርት፣ ድንችና የአትክልት ምርቶች እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንና ሌሎችም መሰረታዊ ሸቀጦች ለማሰራጨት እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ገልጸዋል።
ይህ የአቅርቦት ሥራም አርሶ አደሮችም ሆኑ ማኅበራት በእንቅስቃሴ እገዳው ወቅት ኢኮኖሚያቸውን በመጠኑም ቢሆን እንዲደግፉ ጭምር የተጀመረ መሆኑን አመልክተዋል።
በአማራ ክልል ሁለት ግለሰቦች የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ከተረጋገጠ በኋላ በተለይ በአዲስ ቅዳም፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊና በባህር ዳር ከተሞች ለ14 ቀናት ማንኛውንም ዓይነት የተሽከርካም ሆነ የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ መወሰኑ ይታወሳል።
ይህንንም በተመለከተ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ በቫይረሱ ምክንያት የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው "እስከ ትላንት ድረስ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ሪፖርት እንደደረሳቸው እና ማህበረሰቡም እየተጋገዘ" መሆኑን ጠቁመዋል።
በአራቱ ከተሞች ማንኛውንም ዓይነት የተሽከርካም ሆነ የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ቢወሰንም ወደ ባህር ዳር የሚደረግ የአውሮፕላን በረራ እስካሁን እንደቀጠለ ነው።
"የአውሮፕላን ጉዞን በተመለከተ የሚወስነው ፌደራል መንግሥት ነው" ያሉት ዶ/ር ፋንታ በአውሮፕላን ማረፊያው ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ግን በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በቀን እስከ አምስት የነበረው ወደ ባህር ዳር የሚደረግ በረራ አሁን ወደ አንድ ዝቅ ማለቱን ጠቁመው በዚህም "ቁልፍ ሥራ" የሚያካሂዱ ሰዎች እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
በከተሞቹ ማንኛውንም ዓይነት የተሽከርካም ሆነ የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የተላለፈው ውሳኔ እስከመቼ እንደሚቆይ ሲናገሩም "ይቀጥላል አይቀጥልምን አሁን መወሰን አንችልም። የተዘጋበት ዋናው ምክንያት ቫይረሱ ስለተገኘ ነው" ብለዋል።
በዚህም በ14 ቀናት ውስጥ ምልክት ያሳዩ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ለማስገባት የታመሙም ካሉ ህክምና ለመስጠት ነው።
ውሳኔው ህይወት ለማቆየት የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ውሳኔው ይቀጥል አይቀጥል በሚለው ላይ ለመወሰን 14ቱ ቀናት ተጠናቀው "የህክምና ቡድን የሚሰጠውን ምክር እንከተላለን፤ ከማኅበረሰቡም ጋር እንወያያለን" ብለዋል።