ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮናቫይረስ ዘመን እጅግ ተፈላጊው መሣሪያ፤ ቬንትሌተር
የዓለም መንግሥታት የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ጉዳይ እንዲህ ያስጨነቃቸው ለምንድነው?
በዚህ ወቅት በዓለም አንድ እጅግ ተፈላጊ ምርት አለ። የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ወይም ቬንትሌተር ይባላል።
ይህንን መሣሪያ ከትራምፕ እስከ ሞዲ፣ ከጁሴፔ ኮንቴ እስከ ሩሃኒ፣ ከማክሮን እስከ ማዱሮ በጥብቅ ይፈልጉታል። ለምን?
መልሱ አጭር ነው። ለመተንፈስ።
በሌላ አባባል ይህ መሣሪያ በበቂ የሌላቸው አገራት የሕዝባቸውን ጥቂት የማይባል ቁጥር ሊያጡ ይችላሉ።
ምክንያቱም በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው በሽታው ሲጠናበት ከሁሉ በላይ ለመተንፈስ ይቸገራልና ነው።
በቬንትሌተር ካልታገዘ ደግሞ መዳን እየቻለም ቢሆን ይቺን ዓለም ይሰናበታል።
የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያው የሚሰራው እንዴት ነው?
በአጭሩ ለማስረዳት ቬንትሌተር የሰውነታችንን የአተነፋፈስ ሥርዓት ተክቶ የሚሠራ ማሽን ነው። ሳምባችን እክል ሲገጥመው ነፍሳችን ከመሰወሯ በፊት ይህ ቬንትሌተር ከተገጠመልን ዕድሜ ቀጥል ይሆናል። ምክንያቱ ሌላ አይደለም፤ በቬንትሌተሩ ምክንያት የመተንፈስ ተግባር ስለሚሳለጥ ነው።
ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከል 80 ከመቶው በሽተኞች የሆስፒታል ውስብስብ ክትትል ሳያሻቸው ሊድኑ ይችላሉ።
ነገር ግን ከ6ቱ በሽተኞች ቢያንስ አንዱ የመተንፈስ ችግር ይገጥመዋል። ይህም የሚሆነው ቫይረሱ ሳምባን ስለሚያውክ ነው። በዚህ ወቅት ቬንትሌተር ከሌለ ግለሰቡን ማዳን የማይታሰብ ነው።
ሁለት ዓይነት የሳምባ መርጃ መሣሪያ (ቬንትሌተር) አለ።
በሕክምና ሁለት ዓይነት መተንፈሻ መርጃ መሣሪያ አለ። አንዱ መካኒካል ቬንትሌተር ነው። ሌላኛው ደግሞ ቱቦ-አልባ ቬንትሌተር ይሰኛል።
መካኒካል ቬንትሌተር የአየር ቱቦ በአፍ በኩል እንዲገባ ተደርጎ ታማሚው ካርቦንዳይኦክሳይድ እንዲያስወጣና ኦክሲጅን እንዲያስገባ የሚያደርግ ነው።
ቱቦ-አልባው ቬንትሌተር ወይም በእንግሊዝኛው (Non Invasive Ventilator) ግን ወደ ሳምባ የሚወርድ ቧንቧ ሳይኖረው አፍና አፍንጫ ላይ በሚደረግ ጭምብል ብቻ የሚሰራ ነው።
ቬንትሌተሮቹ ሂሙዲፋየር [እርጥበት የሚፈጥር] ክፍል አላቸው። ይህም ማለት ወደ ሰውነት የሚገባን ሙቀትና እርጥበት የሚቆጣጠርና ሁኔታው ለሰውነት ሙቀት ተስማሚ በሆነ መጠን እንዲሆን የሚያደርግ ነው።
በዚህ ወቅት በሽተኞች የመተንፈሻ አካል ጡንቻዎች ዘና እንዲሉላቸው የሚያስችል መድኃኒት ይሰጣቸዋል።
መጠነኛ የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን የሚያሳዩ በሽተኞች ግን የፊት ጭምብል ቬንትሌተር ብቻ ሊሰጣቸው ይችላል። ይህም በአፍና አፍንጫ በኩል በግፊት አየር ወደ ሳምባ እንዲገባ የማድረግ ዘዴ ነው።
እንደ ኮፍያ የሚጠለቀው ቬንትሌተር
የለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ መሐንዲሶች ከመርሴዲስ ፎርሙላ-1 አቻዎቻቸው ጋር በመሆን አዲስ ዓይነት አጋዥ የመተንፈሻ መሣሪያ ለመሥራት ሙከራ ላይ ናቸው።
ነገሮች በታሰበው መልኩ ከሄዱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በቀን 1ሺ የመተንፈሻ መሣሪያን ማምረት ይችላሉ። ይህ ለእንግሊዛዊያን ነው።
ይህ አዲሱ ምርት እንደ ኮፍያ የሚጠለቅና መላው ፊትን የሚሸፍን ነው።
በሰሜን ጣሊያን ሎምባርዲ በኮቪድ-19 በተያዙ በሽተኞች ላይ በተደረገ ሙከራ 50 ከመቶ የሚሆኑት ከአፍ ወደ ሳምባ የሚወርድ የአየር ትቦ ማስገባት ሳያስፈልጋቸው በዚህ አዲሱ የመተንፈሻ መሣሪያ (የትንፋሽ ኮፍያ) መተንፈስ ይቻላቸዋል ተብሏል።
ይህ በጭንቅላት የሚጠለቀው አዲሱ የመተንፈሻ ኮፍያ ቫይረሱ ከበሽተኞች ትንፋሽ ጋር አየር ላይ ለደቂቃም ቢሆን እንዳይቆይ ስለሚያስችል ተመራጭ አድርጎታል።
ሁሉም ዓይነት የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያዎች በባለሞያ ካልታጋዙ ድንገተኛ ሞትን የሚያስከትሉ ናቸው።
አገራት ስንት መተንፈሻ መሣሪያ ያስፈልጋቸዋል?
የእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት (NHS) ለጊዜው በእጁ የሚገኘው የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ቁጥር 8175 ብቻ እንደሆነ ይፋ አድርጓል። ይህ ቁጥር እየመጣ ካለው አደጋ አንጻር ሲነጻጸር በጣም ትንሽ ነው።
በትንሹ 30 ሺህ ያህል ያስፈልጋል። ይህን ቁጥር ለማሳካት በእንግሊዝ ትልልቅ ኩባንያዎች እየተረባረቡ ነው።
በእንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ሌላ ቁሳቁስ አምራጭ ድርጅቶች ሳይቀሩ "ዳይ ወደ ቬንትሌተር ምርት ግቡ!" ተብለዋል።
በእንግሊዝ ከሁሉም ትኩረት የሳበው በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና በኪንግስ ኮሌጅ ሳይንቲስቶችና መሐንዲሶች ጥምረት እውን ሊሆን የተቃረበው ባለ ርካሽ ዋጋ የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ነው።
ህንድ
በህንድ 1.3 ቢሊዮን ሕዝብ ቤቱ እንዲጸና ከተደረገ በኋላ ክፉ ቀን ሊመጣ ነው በሚል የቬንትሌተር ምርት ተጧጡፏል። በተለይም ወጣት መሀንዲሶች ኪስ የማይጎዳና ቶሎ ሊደርስ የሚችል የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ለመፍጠር ቀን ተሌት እየሠሩ ነው።
ህንድ ለዚህ ሁሉ ሕዝቧ ያላት የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ቁጥር 48 ሺህ ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉ በትክክል እንደሚሰራ እንኳ የሚያውቅ የለም።
አሜሪካ
አንድ የካሊፎርኒያ ኩባንያ ከዚህ በፊት አገልግሎት ላይ የነበሩና የተበላሹ የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያዎችን መልሶ በመጠገኑ እየተሞካሸ ነው። ብሉም ኢነርጂ የተባለው ይህ ኩባንያ 170 ቬንትሌተሮችን ነው አድሶ ወደ ሥራ የሚያስገባው።
ቴስላ በበኩሉ 1255 የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያዎችን ከ3 የተመሰከረላቸው አምራች ኩባንያዎች በመግዛት ለኒው ዮርኩ አስተዳዳሪ አስረክቧል።
የኒው ዮርኩ ገዢ ለስጦታው አመስግነው በቀጣይ ሳምንታት እነዚህ መሣሪያዎች በርካታ ሕይወትን ይታደጉልናል ብለዋል። ኒው ዮርክ እስከ 30 ሺህ የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ያስፈልጋታል።
መኪና አምራቹ ቴስላ ብቻ ሳይሆን ጄኔራል ሞተርስ እና ፎርድም ይህንን እጅግ አስፈላጊ የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ በማምረት ተጠምደዋል።
ሶሳይቲ ኦፍ ክሪቲካል ኬር ሚዲስን እንዳለው ከሆነ አሜሪካ እስከ 960 ሺህ የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያዎች ሊያስፈልጋት ይችላል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በጤና ዘርፍ ብዙ ርቀት ያልሄዱ አገራት ትልቅ ፈተና ይኸው መሣሪያ እንደሚሆን ይታሰባል። ምክንያቱም ከ6ቱ ታማሚዎች አንዱ በዚህ ቬንትሌተር ካልታገዘ ሕይወትን ማቆየት ከባድ ነውና። አይበለውና በርካታ ሰዎች በኮቪድ 19 ቢያዙ አገሪቱ ያላት የቬንትሌተር ቁጥር በበቂ ሊዳረስ አይቻለውም።
ብዙ አገራት ያሏቸው ቬንትሌተሮች ያረጁና ለዚህ በሽታ የማይመጥኑ ናቸው እየተባለ ነው። እነሱም ቢሆኑ በሌሎች በሽታዎች በሚሰቃዩ ሰዎች ተይዘዋል።
ማሊ የሕዝቧ ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ያሏት የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያዎች ግን 56 ናቸው።