ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዘመኑ ህጻናት የወደፊት እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ተባለ
ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እንደሚለው ህጻናት ጤናማ በሆነ መልኩ እንዲያድጉና የተጣለባቸው ተስፋ ላይ በአግባቡ እንዲደርሱ ምቹ አካባቢን መፍጠር ላይ አገራት ወደኋላ ቀርተዋል።
የአየር ጸባይ ለውጥ፣ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ፈጣን ምግቦች በስፋት መተዋወቅና ገና በልጅነት አልኮል መጠጦችን ማዘውተር የዘመኑን ልጆች የወደፊት ተስፋ ስጋት ውስጥ ከቶታል ብለዋል የዘርፉ ባለሙያዎች።
የዓለም ጤና ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ፈንድ 'ዩኒሴፍ' በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ 180 አገራትን ለህጻናት ምቹ መሆን አለመሆናቸውን ለይተዋል።
ለዚህም እንደ ትምህርት፣ አመጋገብ፣ የህጸናት ሞት እንዲሁም የአየር ጸባይ ለውጥን የመሳሰሉ ሁኔታዎች እንደ መስፈርትነት ተቀምጠዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አገራቱ ወደ ከባቢ አየር በሚለቁት የካርቦን መጠንም ተለይተዋል።
አገራት አሁን እየተስተዋሉ የሚገኙ አካሄዶችን ለማስተካከል ጥረት የማያደርጉ ከሆነ ባለፉት 20 ዓመታት የሰው ልጅ ያስመዘገባቸው እምርታዎች ፍሬ አልባ እንደሚሆንና ሁሉም ነገር ወደ ኋላ መመለስ እንደሚጀምር ሪፖርቱን ለማዘጋጀት የተሳተፉት 40 የሚሆኑ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።
''በዓለማችን ዙሪያ የሚገኙ ህጻናት በአየር ጸባይ ለውጥና በተለዋዋጭ የማስታወቂያ መንገዶች ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብተዋል'' ይላሉ የቀድሞ የኒውዝላንድ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጥናቱ ተሳታፊ።
''አገራት በህጻናትና በታዳጊዎች ላይ ያሏቸውን የጤናና የአስተዳደግ ፖሊሲዎች መልሰው መከለስና ቢቻል ሙሉ በሙሉ ለውጥ ማድረግ አለባቸው፤ ምክንያቱም እነዚህ ህጻናት ናቸው የወደፊቱ ተስፋዎች።''
የአየር ጸባይ ለውጥ፣ እንደ ሰደድ እሳት፣ አውሎ ነፋስና ጎርፍ የመሳሰሉ ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የምግብ እጥረት እንዲሁም እንደ ወባ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች የዓለማችንን ህጻናት መጻኤ ተስፋ ጥያቄ ውስጥ እያስገቡ ስለመሆኑ መረጃ መሰብሰብ እንኳን አያስፈልግም ብለዋል ባለሙያዎች።
'' ከሁለት ቢሊየን በላይ የሚሆኑ የዓለማችን ህዝቦች እድገት እንዳያስመዘግቡ በሰው ሰራሽ ቀውሶች፣ እርስ በርስ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና እጅግ አስፈሪ እየሆነ የመጣው የአየር ጸባይ ለውጥ እንቅፋቶች ሆነዋል'' ይላሉ ሌላኛዋ የቡድኑ አባል የሆኑት የሴኔጋሏ ሚኒስትር አዋ ኮል ሴክ።
የዓለማችን ደሃ የሚባሉት አገራት የካርቦን ልቀታቸው እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ከአየር ጸባይ ጋር በተያያዘ ከሚመጡ ችግሮችና አደጋዎች ህጻናቶቻቸው የተጠበቁ ናቸው። ነገር ግን ድህነት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋዎችና ተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ስጋት ሆነዋል።
በአጠቃላይ ከህጻናት እድገት ጋር በተገናኘ በአብዛኛው የዓለማችን ክፍል እየተስተዋለ የሚገኘው ደግሞ የማስታወቂያዎች ብዛት ነው።
አንድ ጥናት በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው የዘመኑ ህጻናት በዓመት እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን የሚመለከቱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ የአልኮል መጠጥ፣ ፈጣን ምግቦችና ጣፋጭ መጠጦች ናቸው።
ለቴሌቪዥን ብዙም ቅርበት የሌላቸው እንኳን በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት በእድሜያቸው ተገቢ ያልሆነ ማስታወቂያዎችን በቀላሉ ይመለከታሉ። ማህበራዊ ሚዲያዎች ደግሞ ከማስታወቂያዎች ባለፈ በርካታ ያልተጣሩና እድሜያቸውን ያላገናዘቡ መረጃዎችን ያገኛሉ።
እነዚህ ነገሮች ምናልባት ቀላል መስለው ሊታዩ ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን የልጆቻችንን አስተዳደግና ጤና በእጅጉ እየጎዱ የሚገኙ ገሮች ናቸው።
ሪፖርቱ በአጠቃላይ የሚከተሉት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ሃሳቦችን አቅርቧል።
- ለህጻናት ምቹ ዓለምን ለመፍጠር የካርበን ልቀትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ
- ዘላቂነት ያለው እድገትን ለማስመዝገብ ህጻናትና ታዳጊዎችን ማዕከል አድርጎ መስራት
- በአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ላይ በርከት ያለ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ ማድረግ
- ከህጻናት አስተዳደግና ጤንነት ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ አዳዲስ ፖሊሲዎችና ህጎችን ማርቀቅ
- ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶች የሚተዋወቁበትን መንገድ ማስተካከል (በአይነትና በመጠን)
በአውሮፓውያኑ 2019 የተሰራ አንድ ሌላ ጥናት እንደጠቆመው በዓለማችን ሚገኙ 2.3 ቢሊየን ህጻናትና አዋቂዎች ከመጠን በላይ የወፈሩ ሲሆኑ ከ 150 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህጻናት ደግሞ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ እድገት አሳይተዋል።
ይህ ደግሞ ህጻናቱ ማደግ ከሚገባቸው ፍጥነት ወይ ወደኋላ ናቸው አልያም ተገቢ ባልሆነ ፍጥነት አድገዋል ማለት ነው።