ወደቻይና የተጓዙና የኮሮናቫይረስ ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች ተገኝተው ነበር ተባለ

የኮሮና ቫይረስ በሽታ ስጋት ይፋ ከተደረገ በኋላ ባለፉት 25 ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ 17 የበሽታው ምልክቶች የታየባቸውና የቻይና ጉዞ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ተገኝተው እንደነበር የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትውት አስታወቀ።

እነዚህ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎችም በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ በማቆየት በተደረገላቸው የላቦራቶሪ ምርመራ 17ቱም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ከማቆያው እንዲወጡ ተደርጓል ተብሏል።

መስሪያ ቤቱ ጨምሮም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከ146 ሺህ በላይ መንገደኞች ላይ የሙቀት መለካት መደረጉንና ከእነዚህ ውስጥም ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገራት የመጡ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ባለፉት 25 ቀናት ውስጥ 60 የሚደርሱ የበሽታው ጥቆማዎች ለሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰው ከእነዚህም ውስጥ 17ቱ የበሽታው ምልክቶችን በማሳየታቸው በሁሉም ጥቆማዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ከበሽታው ነጻ መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህም እስካሁን ባለው መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ በሽታ ያለበት ሰው እንዳልተገኘ መግለጫው ጠቅሷል።

በመግለጨው ላይ እንደተመለከተው አንድ ግለሰብ የበሽታው ምልክት ታይቶበት በሽታው እንደሌለበት እስኪረጋገጥ ድረስ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ የህክምና ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ በመረጋገጡ ከማዕከሉ እንዲወጣ ተደርጓል።

መግለጫው አክሎም የኮሮናቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ካለባቸው አገራት የመጡ ሰዎች ሊያደርጉ የሚገቧቸውን ጥንቃቄዎችም አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት ራሳቸውን ከቤተሰባቸውና ከሌሎች ሰዎች ለ14 ቀናት በማግለል ጤናቸውን እንዲከታተሉ እንዲሁም በየዕለቱ የጤናቸውን ሁኔታ ለመከታተል ለሚደውሉ ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቋል።

በተጨማሪም ትኩሳት፣ ሳልና የመተንፈስ ችግር ካጋጠመ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ማግኘት እንዳለባቸውና በሚያስሉበት እንዲሁም በሚያስነጥሱበት ጊዜ አፍና አፍንጫን ክንድን በማጠፍ ወይም በሶፍት መሸፍን፤ በተጨማሪም እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ እንደሚያስፈልግ መክሯል።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው እስካሁን ድረስ 1775 ሰዎች በበሽታው ሲሞቱ 26 አገራት ከ71 ሺህ በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ሪፖርት አድርገዋል።