በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሙሽሮች ያልታደሙበት የሠርግ ድግስ

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED BY JOSEPH YEW
ሁሌም የሠርግ ዝግጅቶች እንደታቀዱት አይከናወኑም፤ እየጨመረ የመጣው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ አንድ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን ሙሽራውና ሙሽራዋ በሌሉበት እንዲካሄድ አስገድዷል።
ሙሽሮቹ ጆሴፍ ይውና ባለቤቱ ካንግ ቲንግ ከሠርጋቸው ቀን ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው ነበር ከቻይና ወደ አገራቸው የተመለሱት።
በዚህም ሳቢያ ሠርጉ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት ሰዎች በሥነ ሥርዓቱ ለመታደም ስጋት እንዳላቸው በመግለጻቸው፤ ሙሽሮቹ የእንግዶቹን ፍርሃት ለማስወገድ አንድ ዘዴ ፈጠሩ።
በዚህም ሙሽሪትና ሙሽራው የደስታቸውን ዕለት አብረዋቸው እንዲያሳልፉ የጋበዟቸው እንግዶች ከሚገኙበት አዳራሽ ርቀው ምስላቸውን በቀጥታ በማስተላለፍ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ፈጽመዋል።
ጥንዶቹ ከወዳጅ ዘምድ ርቀው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ማድረግ የሚጠበቅባቸውን በሙሉ ሲያከናውኑና ንግግር ሲያደርጉ በቪዲዮ አማካይነት በአዳራሽ ውስጥ ተቀምጠው ለጠበቋቸው ታዳሚዎች ታይተዋል።
ሴንጋፑር ውስጥ እስካሁን በበሽታው የተያዙ 28 ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህም ከቻይና ውጪ ከፍተኛ ተጠቂዎች ካለባቸው አገራት መካከል ከጃፓን ቀጥላ ሁለተኛ እንድትሆን አድርጓታል።
ምን አማራጭ አለ?
ከቻይና ሁናን ግዛት የመጣችው ሙሽሪት ካንግ ከቤተሰቧ ጋር አዲስ ዓመትን ለማክበር ከሳምንታት በፊት ወደ አገሯ ስትሄድ ሙሽራው ይውም ተከትሏት ሄዶ ነበር።
ሁናን ግዛት ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተነስቶባታል የምትባለው ግዛት ጎረቤት ናት።
ሙሽራው ይው ለቢቢሲ እንደተናገረው በተለይ የሄዱበት የሁናን ግዛት አካባቢ በጣም ገጠር በመሆኑ የተነሳ ስለበሽታው ምንም አይነት ፍርሃት አልነበረም።
ከዚያም ጥንዶቹ ለጥቂት ቀናት በመቆየት በዓሉን አክብረው በሁለት ቀናት ውስጥ በማዕከላዊ ሴንጋፑር ውስጥ በሚገኘው ኤም ሆቴል ውስጥ በደገሱት ሠርጋቸው ላይ ለመገኘት ተመለሱ።
በእርግጥ ጥንዶቹ ጋብቻቸውን የፈጸሙት በጥቅምት ወር ላይ በሙሽሪት አገር ቻይና ውስጥ ሲሆን እዚያም ደግሰው እንግዶቻቸውን ጋብዘዋል።
ይህ ሴንጋፑር ውስጥ ያዘጋጁት ሁለተኛው ትልቁ የዕራት ግብዣ በመጀመሪያው ላይ ወደ ቻይና ሄደው ሠርጉን ለመታደም ያልቻሉ የሙሽራውን ቤተሰብ አባላት ለመጋበዝ የተዘጋጀ ነበር።
በእስያ ውስጥ ሁለት የሠርግ ሥነ ሥርዓቶችን ማዘጋጀት ብዙም ያልተለመደ አይደለም። በተለይ ደግሞ ጥንዶቹ ከሁለት የተለያዩ አገራት የመጡ ከሆነ በተለያዩ ቦታዎች ድግስ ይኖራል።

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED BY JOSEPH YEW
የታዳሚው ስጋት
በሠርጉ ላይ እንዲታደሙ የተጠሩት ሰዎች ሁለቱ ጥንዶች ከቻይና መመለሳቸውን ሲሰሙ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የመገኘታቸው ነገር እያሳሰባቸው መጣ።
"አንዳንድ ጥሪ የተደረገላቸው ሰዎችም እንደማይመጡ መናገር ጀምረው ነበር።" ይላል ሙሽራው።
"እኛም የሠርጉን ሥነ ሥርዓት ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ፈልገን የነበረ ቢሆንም፤ ሆቴሉ ሁሉም ነገር መዘጋጀቱንና ምንም ድርድር እንደማይኖር በመግለጽ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በዚህም ምንም አማራጭ ስለሌለን በዕቅዳችን መሰረት ሠርጋችንን ለማከናወን ወሰንን።"
የሠርጉን ታዳሚዎች ፍርሃት ለማስወገድም ጥንዶቹ እንግዶቹ በሚገኙበት ሥፍራ ላይ ላለመገኘት ወሰኑ።
"ይህንን ለታዳሚዎቹ ገልጸን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ሠርጉን እንደምንታደም ስንነግራቸው አንዳንዶቹ ደነገጡ" የሚለው ሙሽራው ያው፤ "አዳራሹ ውስጥ ብንሆን ኖሮ የሚኖረው ድባብ የተለየ ይሆን ነበር፤ ታዳሚዎቹ ስለበሽታው በማሰብ ይጨነቁ ነበር" ብሏል።
"መጀመሪያ ላይ ቤተሰቦቼ በሃሳቡ ደስተኛ አልነበሩም፤ ነገር ግን ቆይተው ተስማምተውበታል።"
ከቻይና መምጣት የነበረባቸው የሙሽሪቷ ካንግ እናት በቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት በተፈጠረ ስጋት ምክንያት በተጣለ ተደራራቢ የጉዞ እገዳ ሳቢያ በሠርጉ ላይ መገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED BY JOSEPH YEW
ሠርግ በቪዲዮ ኮንፈረንስ
በመጨረሻም ለሠርጉ ከተጋበዙት 190 ሰዎች መካከል 110ሩ በዝግጅቱ ላይ ለመታደም የቻሉ ሲሆን፤ ሌሎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይገኙ ቀርተዋል።
በሠርጉ ዕለት ምሽት የተጠሩት ከአንድ መቶ በላይ እንግዶች በሆቴሉ አዳራሽ ውስጥ ሆነው ሙሽሮቹ ደግሞ በሆቴሉ አንድ ክፍል ውስጥ በመሆን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ምስላቸው በትልቅ የሸራ ስክሪን ላይ እየታየ አስፈላጊውን ሥነ ሠርዓት ሁሉ አከናውነው ከታዳሚው ጋር ደስታቸውን ተጋርተዋል።
"ጠሪ አክብረው የመጡትን እንግዶች አመስግነን የተዘጋጀውን እራት እየበሉ እንዲዝናኑ ጋብዘናቸዋል" ይላል ሙሽራው ይው።
ሆቴሉም ለጥንዶቹ ሻምፓኝ ያቀረበላቸው ሲሆን እነሱም ክፍላቸው ውስጥ ሆነው ክዳኑን አፈናጥረው በመክፈት ጽዋቸውን አንስተው ለታዳሚው የምስጋና ንግግር አድርገዋል።
ይህ ሙሽሮቹ በአንድ ክፍል ውስጥ ሆነው ያከናወኑት ሥነ ሥርዓት በሙሉ በአዳራሽ ውስጥ ሆነው ሠርጉን ለታደሙት እንግዶች በቪዲዮ በቀጥታ ተላልፏል።
"በዚህ ሁኔታ አላዘንንም፤ ነገር ግን ቅር ብሎናል" ሲል ሙሽራው ይው ለቢቢሲ ተናግሯል።
አክሎም "ምንም አይነት ምርጫ አልነበረንም፤ ስለዚህም የሚጸጽተን ነገር የለም።"












