ተገድለዋል ሲባሉ የነበሩት የኪም አክስት በቲቪ መታየታቸው እያነጋገረ ነው

የሰሜን ኮሪያው ሞገደኛ መሪ ኪም ጆንግ ኡን አክስት በቲቪ መታየታቸው ዓለምን እያነጋገረ ነው።

ወ/ሮ ኪም ዮንግ ሁዪ በፈረንጆቹ 2013 በኪም ትእዛዝ በአደባባይ የተገደሉት የጃንግ ሶንግ ቴክ ሚስት ነበሩ።

ጎረምሳው ኪም ሰውየውን ከገደላቸው በኋላ የሰውየው ሚስት በአደባባይ ታይተው አያውቁም ነበር። የብዙዎች ግምት ሴትዮዋ እንደ ባለቤታቸው ሁሉ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ወይም ደግሞ ግዞት ወርደዋል የሚል ነበር።

አቶ ጃንግ ሶንግ ቴክ የተገደሉበት ሁኔታ በውል የማይታወቅ ሲሆን አንዳንዶች በአየር መቃወሚያ ነው የተገደሉት ሲሉ ሌሎች ደግሞ ተቀልተው ነው ይላሉ።

በአንድ ወቅት ኢኤንን ኤን ከሰሜን ኮሪያ የከዳ የአይን እማኝን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ አቶ ጃንግ መጀመርያ ሁለት ወዳጆቻቸው በጭካኔ ሲገደሉ እንዲመለከቱ ከተገደዱ በኋላ የወዳጆቻቸው ደም እርሳቸው ገላ ላይ እንዲደፋ ተደርጎ ከዚያ በኋላ ራሳቸውን እንዲስቱ ሆነዋል።

ከጊዜ በኋላም በጽሑፍ ለመግለጽ እንኳ በሚዘገንን አሰቃቂ ሁኔታ ነው የተገደሉት ሲል ዘግቦ ነበር።

ወ/ሮ ኪም ዮንግ ሁዪ የሰሜን ኮሪያ መሥራች አባት የሚባሉት የኪም ኢል ሱንግ ሴት ልጅ ናት። የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ መሪ የኪም ጆንግ ኢል ደግሞ እህት ናቸው። ይህ ማለት ሴትየዋ የፕሬዝዳንት ኪም አክስት ናቸው ማለት ነው።

ባላቸው አቶ ቻንግ ሶነግ ቴክ ደግሞ የኪም የቅርብ ቤተሰብ ነበሩ፤ በፍጹም ባልተጠበቀ ሁኔታ በአገር ክህደት ተከሰው በጎረምሳው ኪም የማያወላዳ ትእዛዝ በአደባባይ የተገደሉት በፈረንጆቹ በ2013 ነበር።

ከዚያች ዕለት ጀምሮ ሚስታቸውን አየሁ ያለ አልነበረም።

ባለፈው እሑድ የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ሴትዮዋን ከኪም ጋር ቁጭ ብለው ሲያጨበጭቡ አሳይቷቸዋል። የታዩትም በአዲስ ዓመት በዓል ላይ በፒዮንግያንግ ቴአትር ቤት ውስጥ ነበር።

ሴትየዋ ከኪም ጆንግ ኡንና ሚስታቸው ጎን ተቀምጠው ነበር የታዩት።

ብዙዎች የሴትየዋን በሕይወት መታየት እንደ ተአምር አይተውታል። በርካታ ሰሜን ኮሪያዊያን ሴትየዋ ወይ ተሰደዋል፣ ወይ ተገድለዋል፥ ወይ ግዞት ላይ ናቸው ብለው ያምኑ ነበር።

ተንታኞች ሴትየዋ በብሔራዊ ቴሌቪዥን መታየታቸው ምናልባት ከኪም ጋር ሰላም ወርዷል፣ የቀድሞው ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውን እንዲሁም አማካሪነታቸውን መልሰው አግኝተውታል ማለት ነው እያሉ ነው።

ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው ሴትየዋ በዚያች አገር መታየት አልፈልግም ብለው ሐዘን መቀመጥ ይቻላቸዋል ወይ? በቲቪ አለመታየትስ ይችላሉ ወይ? ሲሉ ጽፈዋል።

ባለቤታቸውን ካስገደለው ሰው ጋር ጎን ለጎን ቁጭ ብሎ ማጨብጨብ የዚያችን አገር ገዢዎች የጭካኔ ደረጃን ነው የሚያሳየው ያሉም አልጠፉም።

ወ/ሮ ኪም የንግ ሁዪ እና ሟቹ ባለቤታቸው ቻንግ ሶንግ ቴክ የአሁኑ ኪም ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ከ10 ዓመት በፊት ሚናቸው ቀላል አልነበረም።

ጎረምሳው ኪም 2011 አባቱን ተክቶ መንበሩን ሲቆናጠጥ እኚህ የአክስቱ ባል ሚስተር ቻንግ ነበሩ ከሥር ከሥር 'እየቆነጠጡ' የአስተዳደር ጥበብን ያስተማሩት።

ሆኖም ከሁለት ዓመት የቅርብ ክትትልና አማካሪነት በኋላ አብረውት ስብሰባ ላይ ሳሉ በአስደናቂ ሁኔታ በልዩ ኮማንዶዎች ተወሰዱ። የኪም መንግሥት እንደሚለው አጎትየው እሱን ከሥልጣን ለመመንገል ሲያሴሩ ነበር የተደረሰባቸው።

ብዙም ሳይቆዩ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ከውሻ የባሱ ዉሻ በሚል ተሰድበው፤ በጦር ፍርድ ቤት ቀርበው በሞት ተቀጥተዋል።

ሁልጊዜም ቢሆን ከኪም ጎን ይታዩ የነበሩት ቻንግ ሶንግ ቴክ በከሃዲነት በሞት ከተቀጡ ወዲህ በእያንዳንዱ ተንቀሳቃሽም ምሥልም ሆነ ፎቶ ላይ በልዩ ጥበብና አርትኦት እንዲሰረዙ ተደርገዋል። እርሳቸው የሚታዩበትን ምሥል መልቀቀም በዚያች አገር ያስቀስፋል።