ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኩፍኝ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
በዓለም ዙሪያ በኩፍኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከ140 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን አንድ ይፋዊ ግምት አመለከተ።
ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መሆናቸውም ተነግሯል።
የጤና ባለሙያዎች ስለዚህ ክስተት ሲገልጹ በቀላሉ በክትባት መከላከል የሚቻል በሽታ የሰዎችን ህይወት መቅጠፍ መጀመሩ በጣም አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው ብለውታል።
ባለፉት አስራ ዘጠኝ ዓመታት በሽታውን በመከላከል በኩል ትልቅ ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም፤ የኩፍኝ በሽታ ክስተት በተለያዩ ቦታዎች እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል።
ባለፈው ዓመት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አልባኒያ፣ ቼክ ሪፐብሊክና ግሪክ ኩፍኝን ከአገራቸው አስወግደዋል ተብለው የተሰጣቸውን እውቅና አጥተዋል።
በዚህ ባለንበት ዓመትም የኩፍኝ በሽታ ክስተት የበለጠ የከፋ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ከ25 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የተባለ የኩፍኝ ክስተት በአገሯ መኖሩን አሜሪካ ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በማዳጋስካርና በዩክሬን ከፍተኛ ወረርሽኝ መከሰቱም ተነግሯል።
በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘው ሳሞአ የተባለችው አገር ደግሞ በኩፍኝ ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገች ሲሆን የበሽታውን መከላከያ ክትባት ያልወሰዱ ቤተሰቦች የህክምና ባለሙያዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው ቤታቸው ላይ ቀይ ባንዲራ እንዲሰቅሉ አዛለች።
ለበሽታው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መገርሸት እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት መከላከያ ክትባቱን ባለመውሰዳቸው ነው።
ኩፍኝ መስፋፋትን ለማስቆም 95 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት ሁለት ጊዜ የሚሰጠውን ክትባት መውሰድ ይኖርባቸዋል።
ነገር ግን አሃዞች እንደሚያሳዩት ላላፉት በርካታ ዓመታት 86 በመቶ ህጻናት ብቻ የመጀመሪያውን ክትባት ሲወስዱ ሁለተኛውን ክትባት ደግሞ 69 በመቶዎቹ ብቻ ወስደዋል።
ለምን በርካታ ህጻናት ክትባቱን እንዳላገኙ የሚቀርቡት ምክንያቶች የተወሳሰቡ ሲሆኑ፤ ይህም ከአገር አገር የተለያየ ነው።
በተለይ በደሃ አገራት ውስጥ እንደ ዋነኛ ችግር ተደርጎ የሚጠቀሰው የክትባቱ አቅርቦት አለመኖር ነው።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በበሽታው ክፉኛ የተመቱት አምስት አገራት ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ሶማሊያና ዩክሬን ናቸው።
ሌላኛው አሳሳቢ ችግር ደግሞ ክትባቱን ማግኘት እየቻሉ ልጆቻቸው እንዳይከተቡ የሚያደርጉ ወላጆች ጉዳይም ክትባቱ የሚፈለገው ቁጥር ላይ እንዳይደርስ ማድረጉ ተነግሯል።