ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአየር ጸባይ ለውጥ ላይ የሚመክረው ስብሰባ ምን ይዞ ይሆን?
የፖለቲካ መሪዎች እና የአየር ጸባይ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ዲፕሎማቶች እየተባባሰ ስለመጣው የአየር ጸባይ ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ለሁለት ሳምንታት በስፔኗ ዋና ከተማ ማድሪድ ይወያያሉ።
እንደ ተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጻ '' ወደኋላ የማፈግፈጊያ ጊዜ አይደለም፤ ቆራጥ መሆን አለብን'' ብለዋል።
'ሴቭ ዘ ቺልድረን' በበኩሉ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያ ለረሀብ መጋለጥ ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።
አክሎም በከባድ አውሎ ነፋስና ድርቅ ምክንያት 33 ሚሊዮን ሰዎች እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አስቸኳይ የምግብ እርዳታም ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
በቺሊ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ይህ ስብሰባ በሃገሪቱ ባጋጠመው ከፍተኛ አለመረጋጋት ምክንያት ወደስፔኗ ማድሪድ እንዲዘዋወር ሆኗል።
በዚሁ ስብሰባ 29 ሺ የሚደርሱ የሃገራት መሪዎች፣ የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቾችና ሌሎችም ለሁለት ሳምንታት መፍትሄ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ከስብሰባው አስቀድመው መልእክታቸውን ያስተላላፉት የተባባሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል የሀገራት መሪዎችም ቆራጥ መሆን አለባቸው" ብለዋል።
አክለውም '' በጣም ወሳኝ የሆኑ 12 ወራት ከፊታችን ይጠብቁናል፤ በተለይ ደግሞ ዋነኞቹ በካይ ጭሶችን የሚለቁ ሀገራት ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው። የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀትን መቀነስ ላይም ከፍተኛ የሆነ ቆራጥነት ያስፈልጋል።''
''ዝም ብለን ከመቆፈርና ያለውን ሀብት ያለአግባብ ከመጠቀም ይልቅ ታዳሽ የሆኑ ሃይሎችን ተፈጥሮአዊ በሆነና የወደፊቱን ትውልድ በማይጎዳ መልኩ ልንጠቀምባቸው ይገባል'' ብለዋል።
የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት ጥቂት ከሚባሉ ሃገራት በስተቀር ሁሉም ሀገራት ተስማምተው የፈረሙ ሲሆን ከፈረንጆቹ 2020 በፊት ተጨባጭ ሆነ የአየር ንብረት ለውጥን የሚከላከል መፍትሄ ማቅረብ አለባቸው።
አምሳ የሚደርሱ የዓለም መሪዎች በስፔኗ መዲና እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን በስብሰባው እንደማይካፈሉ አስታውቀዋል።