ብራዚል ተዋናይ ሌዎናርዶ ዲካፓሪዮ አማዞን ጫካ እንዲቃጠል አድርጓል ስትል ከሳለች

የብራዚሉ ፕሬዝደንት ጃይር ቦልሶናሮ ተዋናይ ሌዎናርዶ ዲካፕሪዮ የአማዞን ጫካ እሣት እንዲለብስ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ሲሉ ወቀሱ።

ፕሬዝደንቱ ተዋናይ ይህንን ስለማድረጉ ምንም ዓይነት ማስረጃ ባይሰጡም አማዞን ጫካ ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሲወቅሱ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ሰደድ እሣቱን ያስነሱት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የፈለጉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ናቸው ያለው የብራዚል መንግሥት የጠረጠራቸውን በርካታ ሰዎች አሥሯል።

ለአማዞን ጫካ መልሶ መቋቋም 5 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል የገባው ሌዎናርዶ የፕሬዝደንቱን ወቀሳ አስተባብሏል።

አራት በጎ ፈቃደኛ የሰደድ እሣት ተከላካዮች በብራዚል መንግሥት መታሠራቸውን ተከትሎ በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቦልሶናሮ መንግሥትን እየወረፉ ይገኛሉ።

ኢ-መንግሥታዊ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾች የብራዚል መንግሥት ድርጊት ፖለቲካዊና ተፈጥሮ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን ለመፈታተን ያሰበ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

ባለፈው ነሐሴ የሰደድ እሣት ሰለባ የሆነው የብራዚሉ አማዞን ጫካ ጉዳይ ብዙዎችን ያስጨነቀ ሆኗል።

ፕሬዝደንቱ ባለፈው አርብ በመኖሪያ ቤታቸው ሳሉ ነው ወቀሳቸውን የሰነዘሩት። «ሌዎናርዶ ዲካፕሪዮ የሚሉት ሰውዬ ጥሩ ይመስላል አይደል? ገንዘብ ሰጥቶ አማዞንን የሚያነድ።»

«እነዚህ ኤንጂኦ ተብየዎች ምንድነው የሚሠሩት? ጫካውን ያቃጥላሉ ከዚያ ፎቶ ያነሳሉ፤ ቪድዮ ይቀርፃሉ። ዎርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ [WWF] ለምሳሌ ከዲካፕሪዮ ጋር ነው የሚሠራው፤ እሱም 500 ሸህ ዶላር እርዳታ አድርጓል።

በተፈጥሮ ጥበቃ ለተሰማሩ ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ የሚታወቀው ዲካፕሪዮ፤ ምንም እንኳ አማዞን ጫካ ውስጥ የሚሠሩ ድርጅቶች እርዳታ ቢሹም እኔ እርዳታ አላደረግኩም ሲል ወቀሳውን አስተባብሏል።