የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ሐሙስ እንደሚታወቅ ይጠበቃል

ብርቱካን ሚደቅሳ

በሲዳማ ዞን የሚካሄደው የሕዝበ ውሳኔ ውጤት በሚቀጥለው ሐሙስ አመሻሽ ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገለጹ።

ሰብሳቢዋ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት የሕዝበ ውሳኔ ሂደቱ በመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ በኋላ መረጃዎችን የማጓጓዝ እና በፍጥነት የማድረስ ችግር መስተዋሉን ልብ ማለታቸውን ጠቅሰው ይህም ችግር ውጤት በማሳወቂያ ጊዜ ላይ ሊንፀባረቅ እንደሚችል አመልክተዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም ቢሆንም ግን ይህ ክስተት ውጤት የማሳወቂያውን ጊዜ ከአንድ ወይንም ከሁለት ቀን በላይ ያራዝመዋል ብለው እንደማያስቡ ተናገረዋል።

የሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልላዊ አስተዳደር ይሁን ወይስ አሁን ባለበት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ይቀጥል በሚለው የዞኑ ነዋሪ በመጪው ረቡዕ በሚከናወነውን ሕዝበ ውሳኔ ይታወቃል።

በመግለጫቸውም የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 2.3 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ተናግረዋል። የሕዝበ ውሳኔው አስፈፃሚዎች በቁጥር ከስድስት ሺህ በላይ ሲሆኑ እነርሱም በ1692 የምርጫ ጣቢያዎች ተሰማርተዋል።

የድምፅ ሰጭዎች ምዝገባ ከጥቅምት 27 ቀን እስከ ኅዳር 06 ድረስ የተከናወነ ሲሆን ምዝገባውም ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ ከጋዜጣዊ መግለጫው ጋር አያይዞ ያሰናዳው ፅሁፍ ያስረዳል።

አንድ መቶ ስድሳ ያህል ቋሚ አና ተዘዋዋሪ ታዛቢዎች ከሲቪል ማኅበረሰብ የተዘጋጁ ሲሆን የተወሰኑት እስካሁን ያለውን ሒደት በመዘዋወር ሲቃኙ ቆይተዋል ብለዋል ብርቱካን። ከዚህም በተጨማሪ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚወከሉ ታዛቢዎች ይገኛሉ።

ወኪሎችን በተመለከተ ሁለቱም የሲዳማ ዞን ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን እና ካለበት ክልል ጋር እንዲቀጥል የሚጠይቁ ድምፆች እንዲሰሙ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልልን እና የሲዳማ ዞንን ቢጠይቅም የዞኑ አስተዳደር ተወካይ ሲያስቀምጥ ክልሉ ሳይወክል ቀርቷል።

"ይህም ያሳዝናል ብለዋል" ያሉት ሰብሳቢዋ "በሁሉም ጣብያዎች የሲዳማ ዞን ወኪሎች ልኳል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ግን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም፣ ሊልክልን አልቻለም። ከምክር ቤት ቀጥለን አስተዳደሩን ጠይቀናል፣ ተወካይ አልላኩልንም።"

ከዚህም የተነሳ ወደምርጫ ጣቢያዎች የተንቀሳቀሰ አካል ማግኘት የሚችለውን የአንደኛውን ወገን ብቻ ወኪል መሆኑን ጨምረው ተናገረዋል። የሕዝበ ውሳኔ ሒደቱን በደረሰው ሪፖርት እና በመስክ ጉብኝቶች ታዝቧቸው የእርምት እርምጃዎች መካከል የአስተዳደር አካላት እና የአገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በሁለት መቶ ሜትር ርቀት መገኘት የማይገባቸው ሰዎች እንዲሁም የተከለከሉ ምልክቶች መታየት አንደኛው እንደሆነ የምርጫ ቦርድ መግለጫ አመልክቷል።

የሕዝበ ውሳኔው በሚካሄድበት ዕለተ ረቡዕ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ ቀድሞ ተገልፆ የነበረ ሲሆን፤ ይህ የሥራ ክልከላ የግል የንግድ ተቋማትንም እንደሚጨምር ብርቱካን ተናግረዋል።

እንደ ሰብሳቢዋ ገለፃ ለሕዝበ ውሳኔው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከአዲስ አበባ ተነስተው በመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥበቃ እየተደረገለት ወደዞኑ በመምጣት ላይ ነው።

ከፍተኛ የተመዝጋቢ ቁጥር የታየባቸውን የምርጫ ጣቢያዎችን በመለየት ተጨማሪ 175 ጣቢያዎችን ቀደሞ ምዝገባ ከተደረገባቸው ጣቢያዎች ጎን የሚያቋቁም መሆኑን ቦርዱ አሳውቋል።