የትራምፕን መረጃ ያሾለከው 'የሲአይኤ መኮንን' ነው ተባለ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብዙ መሰናክል አልፈዋል። ይህኛው ፈተና ግን ከስከዛሬዎቹ ሁሉ የከፋ ነው ይላሉ ተንታኞች።

የቅድመ ክስ ምርመራ ፋይሉ የተከፈተባቸው ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር አደረጉት የተባለውን 'ያልተገባ' የስልክ ውይይት ተከትሎ ነው።

የድራማው አጭር የጊዜ ሰሌዳ የሚከተለውን ይመስላል፦

ጁላይ 18፡ ትራምፕ የዋይት ሃውስ ረዳታቸውን 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋን የወታደራዊ እርዳታ ለጊዜው ለዩክሬን እንዳይሰጥ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ትዕዛዝ ሰጡ።

ጁላይ 25፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የዩክሬኑን አቻቸውን ለ30 ደቂቃ ያህል በስልክ አነጋገሩ።

ሴፕቴምበር 9፡ ኮንግረሱ አንድ የተጠናቀረ መረጃ ደረሰው፤ መረጃው ትራምፕ ባደረጉት የስልክ ልውውጥ አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት መፈጸማቸውን የሚያትትና አስደንጋጭ ነበር።

የስልክ ልውውጡ መሐል ትራምፕ በመጪው ምርጫ ተቀናቃኛቸው እንደሚሆኑ የሚጠበቁትን ጆ ባይደንን አንዳች ጠልፎ የሚጥልላቸውን የወንጀል ቅንጣት እንዲያፈላልጉላቸው ለዩክሬኑ አቻቸው በውለታ መልክ ሲጠይቋቸው ይሰማል።

የኮንግረስ ኢንተለጀንስ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አዳም ሺፍ የደህንነት መሥሪያ ቤቱን ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጆሴፍ ማጓርን በጥያቄ ማጣደፍ ከመጀመራቸው በፊት በትራምፕና በዩክሬኑ ዜለንስኪ መካከል የተደረገው ቃለ ምልልስ የሚከተለውን ይመስል ነበር ብለዋል፡-

ትራምፕ፦ "ከኛ ምን እንደምትፈልግ ሰማሁ። እኔ ደግሞ በምላሹ ካንተ ትንሽ ውለታ ቢጤ እሻለሁ። በዋናነት ተቀናቃኜን ጭቃ እንድትቀባልኝ ነው የምፈልገው፤ መቼስ ይገባሃል ማንን ማለቴ እንደሆነ....።

ዜለንስኪ፦ "...የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን"

የትራምፕን ስልክ ማን 'ጠለፈው'?

በእርግጥ የትራምፕ ስልክ አልተጠለፈም። ሆኖም ከቅርብ ሰዎቻቸው አንዱ የድምጽ ልውውጡን ይዘት ሳያሾልክ አልቀረም። አልያም በርካታ የዋይት ሃወስ ሠራተኞች መረጃ ያቀበሉት ባልደረባ ሳይኖር አልቀረም።

በመሪዎች መካከል የስልክ ልውውጥ ሲኖር የተለመደው ሥርዓት የሚከተለውን ይመስላል።

የፕሬዝዳንቱ ረዳቶች እና የዋይት ሃውስ ባልደረቦች እንዲሁም የደህንነት መኮንኖች አብረው ይቀመጣሉ።

አብረው ባይቀመጡ እንኳ ባሉበት ክፍል ሆነው ልውውጡን ሊያዳምጡ ይችላሉ። የሥራ መደባቸው ይህንን ለማድረግ የሚያስችላቸው ብቻ ናቸው ታዲያ።

በዋይት ሃውስ የስልክ ልውውጦችን የመቅዳት ባሕል የለም። ሆኖም በአጭር በአጭሩ ማስታወሻ የሚይዙ ረዳቶች ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ይኖራሉ። የስልክ ልውውጦች የጽሑፍ ቅጂና ዋንኛ ጨመቅ በኮምፒውተር ውስጥ ይቀመጣል።

የዋይት ሐውስ ምሥጢረኛው ክፍል 'ሲቺዌሽን ሩም'

ፕሬዝዳንቱ ስልክ የሚደውሉት ከዝነኛው "ሲቺዌሽን ሩም" ነው።

የዋይት ሃውሱ "ሲቺዌሽን ሩም" እንደ ጎርጎሳውያኑ በ1961 የተሠራ ቢሮ ነው። እጅግ ምሥጢራዊ ውይይቶች የሚካሄዱበት የምድር ቤት ሲሆን ከተፈቀደላቸው ባለሥልጣናት ውጭ በየትኛው ደረጃ ያሉ ሹመኞች እንኳ ቢሆኑ እንዲሁ ዘው የሚሉበት ክፍል አይደለም።

ብዙዎቹ እጅግ ቁልፍ የሚባሉ የስልክ ጥሪዎች መነሻም ከዚሁ ክፍል ነው።

ለምሳሌ አገሪቱ እጅግ ወሳኝ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ስታካሄድ መሪዎቹና ከፍተኛ ወታደራዊ የደህንነት መኮንኖች ክትትልና መመሪያ የሚሰጡት ከዚሁ ክፍል ነው።

ለምሳሌ ባራክ ኦባማ የኦሳማ ቢንላደንን ግድያና የመጨረሻ ሰዓት ልብ አንጠልጣይ ድራማን በቀጥታ በተጠንቀቅ የተከታተሉበት ክፍል ይኸው "ሲቺዌሽን ሩም" ነው።

አሁን ጥያቄው ትራምፕ ያደረጉት የስልክ ልውውጥ እንዴት ከዚህ ክፍል ሾለከ የሚል ነው።

ለጊዜው ምሥጢር አውጪው ከየት ሆኖ ይህንን መረጃ አሾለከ የሚለው አልተመለሰም። ከበርካታ የዋይት ሐውስ ሰዎች የተባለውን መረጃ እንዳጠናቀረ ግን ተገምቷል።

ይህ በሁለቱ መሪዎች መሀከል የተደረገውን የድምጽ ልውውጥ ይዘትን አሳልፈው የሰጠው ሰው ማንነት እስካሁን አልተገለጸም። አንድ ሰው ይሁን በርካቶች ምንም የተባለ ነገር የለም።

"ምሥጢሩ ያፈተለከው ከሲአይኤ መኮንን ነው"

ዛሬ ጠዋት (አርብ) እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደዘገቡት የትራምፕን ያልተገባ የስልክ ልውውጥ አጠናቅሮ ለሚመለከተው አካል እንዲሾልክ ያደረገው አንድ የሲአይኤ መኮንን ነው።

መኮንኑ በስም ባይጠቀስም በአንድ ወቅት በዋይት ሐውስ ውስጥ ይሠራ እንደነበር ተመላክቷል።

ይህ በትራምፕ ተግባር ላይ ቅሬታ ያጠናቀረው ግለሰብ የዋይት ሐውስ ሰዎች የትራምፕን ድርጊት ለመሸፋፈን ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም ይላል።

ትራምፕ በበኩላቸው ምሥጢራቸውን አሳልፎ ለዚህ ግለሰብ የሰጠውን የዋይት ሀውስ ባልደረባ ማን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉተዋል። "ይህ ሰው ለሰላዮች ቅርብ የሆነ መሆን አለበት" ሲሉም ተደምጠዋል።

"ማነው የሰጠው ግን? ማወቅ እፈልጋለሁ። መረጃውን ማን እንዳሾለከለት ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ያ ሰው ሰላይ ነው ሊሆን የሚችለው" ሲሉ ትራምፕ የተናገሩትን ድምጽ ሎሳንጀለስ ታይመስ እጄ ገብቷል ብሏል ዛሬ።

በዚህም ንግግራቸው ሌላ የትችት መአት ዘንቦባቸዋል ትራምፕ።

ይህ ቅሬታ አጠናቃሪ እንደጠቆመው የሁለቱ መሪዎች የስልክ ልውውጥ የጽሑፍ ቅጂ በተለመደው የኮምፒውተር ቋት እንዲቀመጥ አልተደረገም። ከዚያ ይልቅ እጅግ ከፍተኛ ምሥጢር በሚጠራቀምበት ሌላ ኮምፒውተር እንዲቆይ ነው የተመረጠው። ይህም ነገሩን ለመደበቅ የተደረገ ነው ይላል።

ዛሬ የወጣው መረጃ እንደሚያሳያው ከሆነ ይህ የሲአይኤ መኮንን የስልክ ልውውጡን በቀጥታ የሰማ ሰው አለመሆኑን ነው። ሆኖም ከተለያዩ ምንጮች የደረሰውን መረጃ ማጠናቀሩንና የደረሱትን መረጃዎች በተለያየ መንገዱን ማመሳከሩን በቅሬታ ዶሴው አብራርቷል።

ስለ ትራምፕ ማን ምን አለ?

የታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ናንሲ ፒሎሲ "ዶናልድ ትራምፕ አገራቸውን በሀቅ ለማገልገል የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ እምነት የሚጣልባቸው ሰው አይደሉም" ብለዋል።

ጆ ባይደን በበኩላቸው "ለጊዜው አገሬ ያላት ፕሬዝዳንት ለሥልጣኔ ለከት የለውም ብሎ የሚያምን ነው" ብለዋል በትዊተር ሰሌዳቸው።

ኤልዛቤት ዋረን በበኩላቸው " ትራምፕ በዋሺንግተን የተጨማለቀው አስተዳደር አንድ ገጽታ ብቻ ናቸው"ሲሉ ጽፈዋል።

ጆ ባይደን እዚህ ጉዳይ ውስጥ እንዴት ገቡ?

የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንትና ቀጣዩ የትራምፕ ተቀናቃኝ ጆ ባይደን በልጃቸው ምክንያት ነው ከዩክሬን ጉዳዩ ጋር የተያያዙት።

ልጃቸው ሀንተር ባይደን ለአንድ የዩክሬን የጋዝ ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ነበር። ትራምፕና ጠበቃቸው ሩዲ ጊሊያኒ ጆ ባይደን በአንዳች የሙስና ተግባር እጃቸውን አስገብተዋል ብለው ያምናሉ።

ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ ለዩክሬን መሰጠት ያለበትን እርዳታ በመያዝ ልጃቸው በቦርድ አባልነት የሚመራውን የጋዝ ኩባንያ ጫና ውስጥ በመክተት እንዲሁም ምርመራ እንዳይደረግበት በማድረግ ለልጃቸው ውለታ ውለውለታል ብለው ይከሳሉ።

ለዚህ ክስ ግን ተጨባጭ መረጃ ቀርቦ አያውቅም።

አሜሪካ ከሥልጣን ያሰናበተው ፐሬዝዳንት አላት?

አሜሪካ በታሪኳ ሁለት መሪዎቿን ከ'ሳ ታውቃለች። ቢል ክሊንተንና አንድሩ ጆንሰን።

ቢል ክሊንትን በጎርጎሳውያኑ 1998 በታችኛው ምክር ቤት ክስ ተከፍቶባቸው በ1999 በሴኔት ውድቅ ሆኖላቸዋል።

ይህ ክስ የፍርድ ሂደትን በማደናቀፍ እና ያን ጊዜ የዋይት ሀውስ ተለማማጅ መኮንን የነበረችውን ሞኒካ ልውኒስኪ ጋር የነበራቸውን ጾታዊ ግንኙነት በተመለከተ ዋሽተዋል በሚል ነው።

አንድሩ ጆንሰን በጎርጎሳውያኑ 1968 የጦር ሚኒስትራቸውን አግባብ ባልሆነ መንገድ አባረዋል በሚል ነው ክስ የተከፈተባቸው፤ እሳቸውም የታችኛው ምክር ቤት ክሱን ወደ ላይኛው ምክር ቤት መርቶባቸው ሴኔት ግን 2/3ኛ ድምጽ ሳያገኝባቸው ቀርቷል።

ሪቻርድ ኒክሰን በ1974 በዋተርጌት ቅሌት ክስ ቢመሰረትባቸውም ቀድመው ሥልጣን ለቀዋል።

አወዛጋቢው ትራምፕ ይህንን ረዥም ሂደት ያለውን የክስ ሂደት ምናልባት በሪፐብሊካኖች በተሞላው ሴኔት የ2/3ኛ የአብላጫ ድምጽ ማጣት ቢያልፉት እንጂ እጅግ ጥልቅ ወደሆነ ቅርቃር ውስጥ ስለመግባታቸው ግን ተንታኞች ከወዲሁ እየተናገሩ ነው።

የትራምፕ መጨረሻ ተቃርቦ ይሆን?