ሴቶችን እያነቀ የሚገድለው ናይጄሪያዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

በናይጄሪያ በየሆቴሉ እየገባ ሴቶችን እያነቀ የመግደል ሱስ ያለበት ሞገደኛ ወንጀለኛ ድርጊቱን አመነ። ለጊዜው "ሲጥ ያደረኳቸው" ሴቶች ብዛት 15 ብቻ ነው ብሏል፤ ለፖሊስ።
መርማሪ ፖሊስ ሙስጠፋ ዳንዳርዋ እንደተናገሩት "ተጠርጣሪው መጀመርያ ላይ 5 ሴቶችን ብቻ ነው ያነቅኩት ብሎን የነበረ ቢሆንም አሁን ከብዙ ምርመራ በኋላ ቁጥሩን 15 አድርሶታል" ብለዋል ለቢቢሲ።
ተጠርጣሪው የተያዘው በርካታ ሴቶች በተመሳሳይ መንገድ እየታነቁ ተገድለው ከተገኙ በኋላ በተደረገ ጥብቅ ክትትል ነው። ሁሉም ሟቾች የተገኙት በሆቴል አልጋቸው ላይ ሳሉ ነው። ብዙዎቹ ደግሞ የናይጄሪያ የነዳጅ ከተማ በሆነችው ፖርት ሃርኮርት ባሉ ሆቴሎች ነው ታንቀው የተገኙት።
የፖሊስ አለቃና መርማሪ አቶ ሙስጠፋ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው በዚያች ከተማ በየሆቴሉ እየወሰደ 9ኙን እንዴት እንደገደላቸው መርቶ አሳይቶናል ብለዋል።
ከዚህች ከተማ ሌላም ብዙ ቦታ ሴቶችን ገድሏል ያሉት እኚሁ የፖሊስ አለቃ በሌጎስ አንድ፣ በኦዌሪ አንድ፣ በሳፔሌ አንድ በአባ አንድ በቤኒንና በኢባዳንም እንዲሁ አንድ አንድ ሴቶችን መግደሉን አምኗል።
ተጠርጣሪው ሴቶቹን ከመግደሉ በፊት እግርና እጃቸውን በተመሳሳይ መንገድ ጥፍር አድርጎ ያስራል። ይህም የድርጊት መመሳሰል ለፖሊስ ምርመራ እገዛ አድርጓል።
ባለፈው ረቡዕ ወንጀለኛው ታድኖ እንዲያዝ ነዋሪዎች አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ ነው ፖሊስ ምርመራውን ያፋፋመው።
የዚህን ሞገደኛ ወንጀለኛ ድርጊት ተከትሎ ሁሉም ሆቴሎች ሲሲቲቪ ካሜራ እንዲገጥሙ እና የተስተናጋጆችን ማንነት መዝግበው እንዲይዙ አዲስ መመሪያ ተላልፎላቸዋል።












