ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በወፍራም ሴቶች የተሳለቀችው የቴሌቪዥን አቅራቢ ከሥራዋ ታገደች
ግብጻዊቷ የቴሌቪዥን አቅራቢ ሬሃም ሳኢድ ያለ ልክ ስለወፈሩ ሰዎች በሰጠችው አስተያየቷ ከሥራዋ ታግዳለች።
የሃገሪቱ ሚዲያ ተቆጣጣሪ ሬሃም በፕሮግራሟ ላይ በግብፅ ያሉ ሴቶችን የሚያስቆጣ ቃላትና ተጠቅማለች ብሏል።
ጋዜጠኛዋ በምታቀርበው የቴሌቪዥን ፕሮግራሟ ላይ "ያለ ልክ የወፈሩ ሰዎች ለቤተሰባቸውም ሆነ ለአገር ሸክም ናቸው" የሚል አገላለፅ ተጠቅማለች።
ጋዜጠኛዋ በግሏ የኢንስታግራም ገጽ ላይ ጡረታ እየወጣች እንደሆነ በማስታወቅ የተባለውን አስተያየት አላልኩም ስትል አስተባብላለች።
ሬሃም አስተያየቱን የተናገረችው ባለፈው ዓመት የአገሪቷ ፕሬዚደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የአገሪቷ ዜጎች ክብደታችሁን ቀንሱ ሲሉ ካስጠነቀቁ በኋላ ነበር። በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ ግብጻዊያን ራሳቸውን መንከባከብ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
በአል ሃያህ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሚተላለፈው የሬሃም 'ሳባያ' በተሰኘው የቴሌቪዥን የውይይት ፕሮግራም ላይ "ለከፋ ውፍረት የተዳረጉ ሴቶች በሰውነታቸው ውስጥ በሚፈጠር የኬሚካል ለውጥ (ቶክሲን) ሴትነታቸውንና ደስታቸውን ያጣሉ" ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
ሬሃም በዚህ አላበቃችም። "ወፍራም ሴቶች ወንዶችን አይማርኩም፤ በመሆኑም ብዙ ጊዜ ወፍራም የሆነችውን ሚስታቸውን ይፈታሉ፤ አሊያም ከእጮኛቸው ጋር ይለያያሉ" ብላለች።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በጋዜጠኛዋ አስተያየት ላይ የትችት ውርጅብኝ አዝነበዋል።
ሬሃም በኢንስታግራም ገጿ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ኢላማ እንደሆነች ገልፃ ጡረታ እየወጣች እንደሆነ አስፍራለች።
"ታክቶኛል! ምክንያቱም ማንም ሰው ሊያንኳስሳችሁ ሲፈልግ በእንናተ ላይ የሚዲያ ዘመቻ ይከፍቱባችሁና የሌለ ወሬ ያስወሩባችኋል። ከዚያም የማታውቋቸውንና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ 200 ወይም 300 ወይም 400 ወይም 500 ሺህ ሰዎች አሉቧልታ እናንተን ይውጣችሏል" ብላለች።
በዚህም ምከንያት ሰልችቶኛል አሁን ልጆቼን የምንከባከብበት ሰዓት ነው ብላለች።
ሬሃም አክላም ላለፉት 12 ዓመታት ከልክ በላይ ውፍረት የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነች ገልጻለች።
የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢዋ መነጋገሪያ ስትሆን ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በአንድ ወቅት የሶሪያ ስደተኞችን ለመጎብኘት ባቀናችበት ወቅት ስደተⶉቹን «ክብረ ቢስ ናቸው» በሚል መግለጿ መነጋገሪያ ሆና ነበር።
በሌላ አጋጣሚም እንዲሁ አንድ በፈጣሪ መኖር የማታምን ሴት በፕሮግራሟ ስለ አስተሳሰቧ ለማናገር ከጋበዘቻት በኋላ ከፕሮግራሙ እንዳባረረቻት ተገልጿል።