ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዘንድሮው ሐምሌ የዓለም ሞቃታማ ወር በመሆን ተመዘገበ
የዘንድሮው የአውሮፓዊያኑ ሐምሌ ወር በዓለም ከተመዘገቡ ሞቃታማ ወራቶች እጅግ የበለጠው ሆኖ መመዝገቡን የሳተላይት መረጃዎች ማረጋገጣቸው ተገለፀ።
ጥናቱ የተካሄደው በአውሮፓ ሕብረት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚሰራው ድርጅት ኮፐርኒከስ ፕሮግራም (C3S) አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል። ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ይህ መሬት ያልተጠበቀና እንግዳ የሆነ ሙቀት እያስተናገደች ስለመሆኗ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው።
ባለፈው ወር በመላ አውሮፓ ከፍተኛ የሆነና የሚጋረፍ ሙቀት የተመዘገበ ሲሆን በቀዝቃዛው የአርክቲክ ሰርክል ሳይቀር ያልተለመደ ከፍተኛ ሙቀት ታይቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ በአውሮፓውያኑ ሐምሌ ወር 2016 ከተመዘገበው የሙቀት መጠን የዘንድሮው ሐምሌ 2019 በ0.04 ዲግሪ ሴልሸስ ብልጫ በማሳየት በጣም ሞቃታማ እንደነበር ተመልክቷል።
ይሁን እንጂ የ2016ቱ የሙቀት መጠን ከዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ባሻገር የኤል ኒኖ የአየር ንብረት ክስተትን ተከትሎ የመጣ በመሆኑ ሞቃታማ እንደነበር ይታወቃል።
አሁን የወጣው መረጃ ሰኔ ወር ላይ ተመዝግቦ የነበረውን የሙቀት መጠን ተከትሎ እንደመጣ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ባወጡት መረጃ አረጋግጠዋል።
እንደ ኮፐርኒከስ ከሆነ፣ በዚህ ዓመት በየወሩ ከተመዘገቡት አራት እጅግ ሞቃታማ ወሮች መካከል ሐምሌ ወር አንዱ ነው።
ይሁን እንጂ አጥኚዎች ይህንን ክስተት በረዥም ጊዜ ሂደት ከሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር አላያያዙትም።
ይልቁንም በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ምክንያት በሚፈጠር የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት አካባቢያዊ ሙቀት እንደተፈጠረና አዲስ ሪከርድ ሳያስመዘግብ እንዳልቀረ በተመራማሪዎቹ መካከል ሰፊ መግባባት አለ።