ደቡብ አፍሪካ በወሮበሎች ላይ ሠራዊቷን ኬፕታውን ውስጥ አሰማራች

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ኬፕታውን ውስጥ በብጥብጥ ወደሚታመሱት አካባቢዎች መሰማራቱ ተነገረ።

ከደቡብ አፍሪካ ትላልቅ ከተሞች አንዷ በሆነችው ኬፕታውን ውስጥ በሚገኙ ሦስት አካባቢዎች ውስጥ ያለመረጋጋት በማጋጠሙ ነው ወታደሮች እንዲሰማሩ የተደረገው።

ከከተማዋ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ከባድ ግጭት በከተማዋ የሚገኙ የወሮበላ ቡድኖች በሚቆጣጠሩት አካባቢ በይገባኛል ሳቢያ የተቀሰቀሰ ነው። ግጭቱን ተከትሎም የበቀል ጥቃት ተባብሷል።

ቅዳሜና እሁድ ፊሊፕ ኢስት በተባለው የከተማዋ አካባቢ በጥይት የተገደሉትን ጨምሮ ከባለፈው ከአርብ ጀምሮ ቢያንስ 20 ሰዎች በግጭቱ ተገድለዋል።

የከተማዋ የፖሊስ ኃይል ኃላፊ የሆኑት ቤኪ ሲሌ፤ የሠራዊቱን በከተማዋ ውስጥ መሰማራትን በተመለተ ሲናገሩ፤ የነዋሪውን ደህንነት ለማስጠበቅ "ለየት" ያለ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል።

"ቤት ለቤት በመሄድ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን እንሰበስባለን፣ የሚፈለጉ ወንጀለኞችን እንይዛለን እንዲሁም የቀሩትና በዋስ ከእስር የወጡ ወንጀለኞችንም በቁጥጥር ስር እናውላለን" ሲሉ የፖሊስ ኃላፊው ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የሚጠበቁት ወታደሮች እስኪደርሱ ድረስ የጦር ሠራዊቱ እስካሁን ባልተሰማራባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው የፖሊስ ኃይል ተሰማርቷል።

ምንም እንኳን የከተማዋ ባለስልጣናትም የነዋሪውን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ ለዓመታት ጥረት ቢያደርጉም፤ ለአጭር ጊዜ ጋብ ከማለት ውጪ በኬፕታውን ውስጥ ከወሮበላ ቡድኖች ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ችግር ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀ ነው።