ስፔን ውስጥ ከኮርማዎች ጋር በተደረገው ሩጫ ሦስት ሰዎች ተጎዱ

ከነውጠኛ ኮርማ ጋር ሲሯሯዙ የነበሩ ሦስት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው።

በስፔን በሚካሄደው ከነውጠኛ ኮርማዎች ጋር የመሯሯጥ ዓመታዊው ሳን ፌርሚን ፌስቲቫል ላይ 2 አሜሪካዊያንና የስፔን ዜጋ ላይ ጉዳት መድረሱን ባለስልጣናት አስታወቁ።

በቀይ መስቀል ህክምና የተደረገላቸው በጠቅላላው ቀላል ጉዳት ያስተናገዱ ሰዎች ቁጥር ወደ 48 እንደሚጠጋ ባለስልጣናቱ ጨምረው አስታውቀዋል።

ፌስቲቫሉ እስከ የፊታችን እሁድ የሚቀጥል ሲሆን ከኮርማው ጋር መሯሯጡ ጠዋት ጠዋት ላይ ይካሄዳል።

በፌስቲቫሉ ላይ የሚሳተፉት ሰዎች ነጭ ልብስ እና ቀይ ስካረፍ በማድረግ በጠባብ ጎዳና ላይ ለ850 ሜትር ከበሬ ፊት በመሮጥ ለኮርማዎች ወደ ተከለለው ቦታ ድረስ ከኮርማው ጋር ይሯሯጣሉ።

በየቀኑ ስድስት ኮርማዎች ይለቀቃሉ በዚህም በርካቶች ጉዳት ይደርስል። ይህ ጥንታዊ ፌስቲቫል ከ1910 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን እስካሁን 16 ሰዎች በኮርማዎች ተወግተው ህይታቸው አልፏል።

ለመጨራሻ ጊዜ አንገቱ ላይ ተወግቶ ህይወቱ ያለፈው ዳኒኤል ሮሜሮ 2009 ላይ ነበር።

ትናንት ጉዳት ያስተናገደው የ46 ዓመቱ አሜሪካዊም አንገቱ ላይ እንደተወጋና ቀዶ ህክምና እንደተደረገለት አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በዚህ ፌስቲቫሉ ላይ ለመሳተፍ በርካቶች ከመላው የዓለማችን ክፍል ወደ ስፔን ያቀናሉ። ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ሁሉ በፌስቲቫሉ ላይ መሳተፍ የሚችል ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ተሳታፊ ሆነው የሚታዩት ግን ወንዶች ብቻ ናቸው።

ከኮርማዎች ፊት የመሯሯጥ ፌስቲቫል በእንስሳት መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ተቃውሞ ይቀርብበታል።