ማክስ 737፡ «ቤተሰቦቼን በኢትዮጵያው አውሮፕላን አደጋ አጥቻለሁ»

«ባለቤቴ ካሮልን አጥቻለሁ፤ ሦስት ልጆቼ ራያን፣ ኬሊንና ሩቢንን አጥቻለሁ። እንዲሁም የባለቤቴን እናትም አጥቻለሁ፤ ብቸኝነት ይሰማኛል። በተለይ ሰዎችን ሳይ. . . ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ወላጆችን ሳይ. . . እኔ ከልጆቼ ጋር መሆን አለመቻሌን ሳስብ። ድምፃቸውን መስማት፤ ፊታቸውን ማየት አለመቻሌን ሳስብ።»

ፖል ንጆሮጌ፤ ሙሉ ቤተሰቡን ያጣው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 ማክስ 737 አውሮፕላን መከስከስ ሳቢያ ነው። አደጋው በአጠቃላይ የ157 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

ፖል አሁን ከጓደኛ ጓደኛ ቤት እየተዟዟረ ይኖራል፤ ወደ ቤቱ መመለስ አልቻለምና። የልጆቹን ጫማ እንኳ ማየት እንደተሳነው ይናገራል። «እግሮቻቸው ይታዩኛል። እኔ ተመልሼ ወደዚያ መሄድ አልችልም» ይላል ዘመዶቹ ቁሳቁሶቹን ሰብስበው እስኪወስዱለት የሚጠብቀው ፖል።

ሰበበኛው ቦይንግ ማክስ 737 በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው ሁለት ጊዜ ነው የተከሰከሰው። የመጀመሪያው ኢንዶኔዥያ ውስጥ፤ ጥቅምት 2011 ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቢሾፍቱ አቅራቢያ መጋቢት 2011 ነው። የሁለቱም አደጋዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት የአደጋው መንስዔ ተመሳሳይ እንደሆነ ያሳያል።

አሁን የአደጋው ተጎጂ ቤተሰቦችም ሆኑ ሌሎች አንድ ጥያቄ ሰቅዞ ይዟቸዋል። ለምንድነው አውሮፕላኑ ችግር እንዳለበት ከታወቀ በረራ እንዳያደርግ ያልታገደው? የሚል።

ክሪስ እና ክላሪስ ሙርም ልጃቸው ዳንኤሌን ያጡት በኢትዮጵያ አየር መንገዱ አውሮፕላን አደጋ ነው። ቶሮንቶ በሚገኘው ቤታቸው አንድ ክፍል ውስጥ የልጃቸው ፎቶ በአበባ ተከብቦ ይታያል።

ልጃቸው ዳንኤሌ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ስትበር የነበረው ናይሮቢ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ 'ኢንቫይሮንመንት ኮንፈረንስ' ላይ ለመሳተፍ ነበር።

የዳንኤሌ ቤተሰቦች ይናገራሉ፤ «ይህ ሊሆን ባልተገባ ነበር። ኢንዶኔዥያ ላይ ከደረሰው አደጋ አምስት ሙሉ ወር እንኳ ሳይሞላው. . . ደግሞ በጣም ደህንነቱ የተጠበቀ ይሉናል። በፍፁም አይደለም። የምንወዳቸውን ሰዎች ሕይወት የቀጠፈ ነው። ምንም ይበሉ ምንም ሕይወታችን እንደ ቀደመው ጊዜ ሊሆን አይችልም።

ምንም እንኳ የሁለቱም አደጋዎች መንስዔ ከአውሮፕላኑ ጋር የተያያዘ መሆኑ ቢጠቆምም የአሜሪካ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሳም ግሬቭስ «ፓይለቶቹ አሜሪካ ቢሠለጥኑ ኖሮ. . .» ሲሉ ጣታቸውን ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች ላይ ቀስረዋል።

«ቤተሰቦቼን ያጣሁት በቦይንግ ቸልተኝነት፣ እብሪተኝነት እና አስተዳደራዊ ዝቅጠት ነው። የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደርም [ኤፍኤኤ] ቢሆን አወሮፕላኑን በሥርዓቱ መፈተሽ ነበረበት» ይላል ፖል።

«ምክንያቱም ዕድሉ ነበራቸው። የኢንዶኔዥያው አደጋ ሲደርስ አውሮፕላኑን ከበረራ ማገድ ነበረባቸው። የእኔን ቤተሰቦች ጨምሮ 157 ሰዎች በእነርሱ ደካማ አሰራር ሳቢያ ሞቱ። ሰው በእነዚህ አውሮፕላኖች እየበረረ ሳለ ነው ችግሩን ለመቅረፍ የሞከሩት። ግን ምን ዋጋ አለው የመጋቢቱ አደጋ ደረሰ።»

ናዲያ ሚሌሮን እና ባለቤቷ ሚካኤል ስቱሞ በአሜሪካዋ ማሳቹሴትስ ግዛት ነዋሪ ናቸው፤ ሥፍራው ሰላም የተመላ ነው፤ አረንጓዴ ቦታ። የ24 ዓመቷ ልጃቸው ሳምያ ሮዝ መጋቢት 1/2011 ዕሁድ ጠዋት 3፡00 ገደማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በረራ ቁጥር ኢቲ 302ን ተሳፈረች።

«በጣም አስፈሪ ህልም ይመስላል. . . ትላለች እናቷ ናድያ፤ ሁሌም አንድ ቀን ከህልሜ እንደምነቃ አስባለሁ።»

ናድያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን መክሰከስን ዜና የሰማችው ከቢቢሲ ራድዮ ጣብያ ነበር። ልጇ ሳሚያ በዚያ አውሮፕላን ውስጥ እንዳለችም ታውቃለች። ልጇ ከመሳፈሯ አንድ ሰዓት ቀደም ብላ ስለ አውሮፕላኑ ዓይነት በዋትስአፕ ነግራታለች።

«ዜናውን ስሰማ ያንቀጠቅጠኝ ጀመር። ሰወነቴ ሲንቀጠቀጥ ይሰማኛል ቢሆንም ልቆጣጠረው ተሳነኝ። ዜናውን ቤት ውስጥ ለነበሩ ሰዎች መናገር ተሳነኝ።»

ናዲያ ሚሌሮን እና ባለቤቷ ሚካኤል ስቱሞ የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትን እያገኙ "ለምን ይሆን ከመጀመሪያው አደጋ በኋላ ማክስ 737 ከበረራ ሊታገድ ያልተፈለገው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ተቺዎች ማክስ 737 የተሰኘው የቦይንግ አውሮፕላንን ወደ ገበያ ለማውጣት ጥድፊያ ነበረ ሲሉ ይወቅሳሉ። ኤርባስን ከመሳሰሉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ጋር ለመፎካከር ሲል ነው ጥድፍያ ያበዛው፤ የባለሙያዎች ትችት ነው።

ቢቢሲ ቦይንግ እየደረሰበት ስላለው ወቀሳ ምላሽ አለው ብሎ ቢጠይቅም ድርጅቱ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ቦይንግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች 100 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ያለውም በዚህ ሳምንት ነበር። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተጎጂ ቤተሰቦች የቦይንግን ልገሳ እንደማይቀበሉ ነው የሚናገሩት።

ክሪስ ሙር ቦይንግ በወንጀል ሊከሰስ ይገባል ይላሉ፤ ፖል ንጆሮጌ የቢሺፍቱውን አደጋ ሊከላከሉት የሚገባ ነበር ይላል።

ሰሚ ያላገኙ እና ቤታቸውን ዘግተው በማዘን ላይ ያሉትን ጨምሮ፤ የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ጥያቄ እንዳዘሉ ናቸው።