ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወንዶች የማያወሯቸው አምስት አሳሳቢ ነገሮች
በዓለም ዙሪያ በእያንዳንዱ 40 ሰከንድ አንድ ሰው ራሱን ያጠፋል። ብዙ ጊዜ ራሳቸውን የሚያጠፉት ወንዶች ሲሆኑ ምክንያቱ ደግሞ ያጋጠሟቸውን ችግሮች የማውራት ወይም እርዳታ የመጠየቅ ባህል ስለሌላቸው ነው።
ታዲያ ወንዶች በግልጽነት ሊያወሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንድናቸው?
የማህበራዊ ሚዲያ ሕይወትና እውነታው መጋጨት
ማህበራዊ ሚዲያ የአዕምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና የማሳደር አቅም አለው።
የአሜሪካው ፔንስሎቬንያ ዩኒቨርሲቲ በሰራው አንድ ጥናት ማህበራዊ ሚዲያን አብዝተው የሚጠቀሙ ግለሰቦች ለአዕምሮ በሽታና ጭንቀት የተጋለጡ እንደሆኑ ያሳያል። ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሊሆንም ይችላል።
ከሌላ ጊዜ ባነሰ መልኩ ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም የጀመሩ ሰዎች ይሰሟቸው የነበሩ የብቸኝነትና የድብርት ስሜቶች እንደቀነሱላቸው በጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች ገልጸዋል። የጥናቱ ዋና አስተባባሪና የሥነ አዕምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት መሊሳ ሃንት እንደሚሉት ወንዶች በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያዩዋቸውን ነገሮች ማድረግ አለመቻላቸው ከፍተኛ ጫና ያሳድርባቸዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የምንመለከታቸው አስደሳችና አስገራሚ የሰዎች አጋጣሚዎች አብዛኛውን ጊዜ ከእውነታው የራቁና ሰዎች መሆን አልያም ማድረግ የሚፈልጓቸውን ነገሮች የሚገልጹ ናቸው።
በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የሥነ አዕምሮ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኦስካር ይባራ እንደሚሉት ሰዎች ሰው እንደመሆናቸው መጠን እነሱ ያላቸውን ነገር ከሌሎች ሰዎች ጋር ማወዳደር ይወዳሉ።
'' ራሳቸው እንኳን በማያውቁት ሁኔታ ነው ማወዳደር የሚጀምሩት። ሰዎች ሲዝናኑ ሲመለከቱ እኔስ መቼ ነው የምዝናናው? ሰዎች ከሃገር ውጪ ለሥራ ሲሄዱም ተመሳሳይ ጥያቄ ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ለድብርትና ጭንቀት ስሜት ተጋላጭ ያደርጋል።
ብቸኝነት
ቢቢሲ 'ዌልካም ኮሌክሽን ፈንድ' ከተባለ ተቋም ጋር በመተባባር በሰራው በዓይነቱ ትልቅ የሆነ የሙከራ ጥናት መሠረት ከ16 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ብቸኝነት ይሰማቸዋል።
በአውሮፓውያኑ 2017 በተሰራ አንድ ጥናትም በተለየ መልኩ ወንዶች ከብቸኝነት መላቀቅ እንደሚከብዳቸው ተመልክቷል።
ሴቶች ጓደኝነታቸውን ለማስቀጠል የግድ መገናኘት አይጠበቅባቸውም። ስለቀኑ ውሏቸው በስልክ ማውራት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ለወንዶች ግን ለረጅም ሰዓት ስልክ ማውራትና ስለ ቀን ውሎ መወያየት የማይታሰብ ነው።
እንደውም ወንዶች ጓደኝነታቸውን ለማስቀጠል የግድ መገናኘት አለባቸው። ሰብሰብ ብለው እግር ኳስ ይመለከታሉ አልያም ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ይላሉ። እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን የማያደርጉ ከሆነ ግን ለብቸኝነትና ጭንቀት የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው።
ብቸኝነት ከዚህ ባለፈ ለእንቅልፍ እጦትና ከፍ ሲል ደግሞ ራስን እስከማጥፋት ሊያደርስ ይችላል።
ማልቀስ
ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ማልቀስ ለጭንቀትና ድብርት ፍቱን መድሃኒት ነው። ነገር ግን ወንዶችና ማልቀስ ብዙ ጊዜ አይዋደዱም። በወንዶች ዘንድ ማልቀስ እንደመሸነፍና ደካማነት ተደርጎ ይቆጠራል።
እንግሊዝ ውስጥ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት 55 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 የሆኑ ወጣቶች ማልቀስ ወንድነትን ዝቅ ማድረግ ነው ብለው ያምናሉ።
ራስ ማጥፋት ላይ በትኩረት የሚሰራው የአውስትራሊያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ኮልማን ኦድሪስኮል እንደሚሉት ወንዶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ውስጣዊ ስሜታቸውን መግለጽ እንደሌለባቸውና ማልቀስ ደካማነት እንደሆነ እየተነገራቸው ነው የሚያድጉት።
''ማልቀስ በሚገባን ሰዓት ማልቀስ፤ ሁሌም ቢሆን ጭንቀትንና ድብርትን የመቀነስ ከፍተኛ አቅም አለው።'' ይላሉ ኮልማን ኦድሪስኮል።
አባወራነት
እንግሊዝ ውስጥ ከሚኖሩ ወንዶች 42 በመቶ የሚሆኑት ከፍቅር ጓደኞቻቸው አልያም ከሚስቶቻቸው ከፍ ያለ ገቢ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያምናሉ።
ወንዶች ሙሉ የቤታቸውን ወጪ መሸፈን እንዳለባቸው የሚያስቡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ጥቂት የሚባል አይደለም። በአሁኑ ሰዓት ገንዘብና ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጭንቀቶች ከሚታሰበው በላይ እየተስተዋሉ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2015 የተሰራ አንድ ጥናት እንዳመላከተው የሥራ አጥነት መጠን አንድ በመቶ በጨመረ ቁጥር ራስን የማጥፋት ቁጥር በ0.79 በመቶ ከፍ ይላል።
አካላዊ መገለጫዎች
ብዙ ጊዜ ሰዎች ሴቶች ብቻ ስለ አካላዊ ቁመናቸው የሚጨነቁ ይመስላቸዋል። ነገር ግን እውነታው ከዚህ በጣሙን ራቀ ነው።
ጆሽ እንግሊዝ ውስጥ በሚገኝ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በሚቀርብ የቴሌቪዥን ውድድር ላይ ሦስተኛ ሆኖ ነው ጨረሰው። አካላዊ እንቅስቃሴ አብዝቶ መስራቱና ስለ ሰውነቱ መጨነቁ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያምናል።
"በባህር ዳርቻዎችና በተለያዩ ቦታዎች ከወገቤ በላይ እራቁቴን ሆኜ ስንቀሳቀስ ከሴቶች አልፎ ወንዶች እንዴት እንደሚመለከቱኝ አያለው። ምናለ እንዳንተ ዓይነት ሰውነት ቢኖረኝ ብለው የሚያወሩኝም አሉ። '' ብሏል።
ወንዶች ሁሌም ቢሆን ከሌሎች ወንዶች በሁሉም ነገር የተሻሉ ሆነው መገኘት ይፈልጋሉ ። አካላዊ ገጽታቸው ደግሞ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል።