ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢቫንካ ትራምፕ አዲስ አበባ ናቸው
የዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ ሴት ልጅና የዋይት ሃውስ አማካሪ ኢቫንካ ትራምፕ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ላይ ትኩረት ያደረገ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በአዲስ አበባ ጀምረዋል።
ኢቫንካ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉብኝታቸው የመጀመሪያ ውሎ የባህላዊ አልባሳት ማምረቻ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፍው እና በሥራ ቦታ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የሚሰራው ፕሮጄክት እ.ኤ.አ 2025 ድረስ እያደጉ ባሉ ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ 50 ሚሊዮን ሴቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
የዶናልድ ትራምፕ ልጅ በመጀመሪያ ቀን ውሏቸው በሴት የሚመራ የአልባሳት ማምረቻ ተቋምን ጎብኝተዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ፖሊሲ አፍሪካን በተመለከተ በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፤ ሽብርን መዋጋት እና የቻይናን ተጽእኖ በቅርብ መከታተል።
ትራምፕ አፍሪካን በሚመለከት ዘግየተው ይፋ ያደረጉት ይህ ፖሊሲ በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም። ከዚህ ቀደም አሜሪካ ስታደርገው እንደቆየችው በአፍሪካ ዴሞክራሲ እንዲዳብር፣ ነጻ እና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እና የሰብዓዊ መብት እንዲጠበቅ ትኩረት መሰጠት አለበት ይላሉ።
ከሁለት ወራት በፊት ይፋ የተደረገው 'ዓለም አቀፍ የሴቶች እድገት እና ብልጽግና' የተሰኘው ፕሮጄክት፣ ለሴቶች ዘረፈ ብዙ ስልጠናዎችን በመስጠት ጥሩ ገቢ የሚያስገኙ ስራዎችን እንዲያገኙ ይሰራል ተብሏል።
ኢቫንካ በመጀመሪያ ቀን ውሏቸው ሙያ ኢትዮጵያ የተሰኘ የአልባሳት ማምረቻ ድርጅትን ጎብኝተዋል። ድርጅቱ ከ16 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ሲሆን ኢቫንካ ትራምፕን የድርጅቱ መስራት ሳራ አበራ አስጎብኝተዋቸዋል።
ይህ ፕሮጀክት 'በዩ ኤስ አይ ዲ' የ50 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይደረግለታል።
ኢቫንካ ትራምፕ በኢትዮጵያ በቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ኢቫንካ ከኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በመቀጠል ወደ አይቮሪኮስት በማቅናት የሴቶችን ኢኮኖሚ በማጠንከር ዙሪያ በሚዘጋጅ ጉባዔ ላይ ይሳተፋሉ።