ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ 25ኛ አመት እየታሰበ ነው
"እንደገና የቤተሰብነት ስሜትን ማደስ ችለናል" ይህንን ንግግር የተናገሩት የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ሲሆኑ ከ800ሺ ሰዎች በላይ በተገደሉበት የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ 25ኛ አመት በሚታሰብበትም ዕለት ነው።
በወቅቱ የአማፂ ቡድን እየመሩ የነበሩት ፖል ካጋሜ የማስታወሻውን ችቦ በመዲናዋ ኪጋሊ አቀጣጥለዋል።
የሩዋንዳን 1/10ኛ ህዝቧ ያለቀበትን የጭፍጨፋ ወቅትም ሩዋንዳውያን በመቶ ቀናት ሀዘን ለማስታወስ አቅደዋል።
አብዛኛዎቹ የሞቱት የቱትሲ ማህበረሰብና ለዘብተኞቹ ሁቱዎች ሲሆኑ የተገደሉትም በሁቱ አክራሪዎች ነው።
"ከ25 አመታት በፊት ምንም አይነት ተስፋ አልነበረም። ድቅድቅ ጨለማ የዋጠን ጊዜ ነበር" በማለት ፕሬዚዳንቱ በጭፍጨፋው ህይወታቸውን ካጡት መካከል 250ሺ ሰዎች በተቀበሩበት የኪጋሊ የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያ ማዕከል ለተሰበሰው ህዝብ ተናግረዋል።
"በዛሬው እለት ብርሀን እያንፀባረቀ ነው። ይሄ እንዴት ተፈጠረ? ሩዋንዳውያን እንደገና የቤተሰብነትን ስሜት አዳብረናል" ብለዋል።
ሩዋንዳ እንዴት እያስታወሰችው ነው?
መታሰቢያው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ሻማ በማብራት የተጀመረ ሲሆን፤ ይህም ለመቶ ቀናት ይቀጥላል።
ሀገሪቷን ለ19 አመታት የመሩት ፖል ካጋሚ በመቀጠልም በኪጋሊ ስብሰባ ማዕከል ንግግር አድረገዋል።
ከዘር ጭፍጨፋው የተረፉት ሰዎች ጥንካሬ የሩዋንዳውያን አልበገሬ ባይነት ማሳያ ነውም ብለዋል።
"የተሳሰረው የህዝባችን እጅ ያገሪቷ ማገር ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ " እርስ በርስ እንደገፋፋለን።የአካልም ሆነ የአዕምሮ ጠባሳ ቢኖርብንም ብቻችንም አይደለንም" ብለዋል።
አክለውም "የአርበኝነት መንፈሳችን ንቁ ነው። ይህ የተደረገው ጭፍጨፋ በጭራሽ አይደገምም"
ከዚህ በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት ተዘጋጅቶ ለቱትሲዎች መጠለያ በነበረው አማሆሮ አለም አቀፍ ስታዲየም የተደረገውን የሻማ ማብራት ስነ ስርአት መርተዋል።
ወደ 2000ሺ የሚጠጉ ሰዎችም ከፓርላመንት ስታዲየም ድረስ በነበረው የእግር ጉዞ ላይ የተሳተፉ ሲሆን፤ የሻማ ማብራት ስርአትም ተካሂዷል።