በደቡብ አፍሪካ መብራት ለምን በፈረቃ ሆነ?

ሀብታም አገር ናት። በኢንዱስትሪ ብዙ ርቀት ተራምዳለች። 'በአፍሪካ አህጉር የምትገኝ አውሮፓ' እየተባለች ትንቆለጳጰሳለች። ለዜጎቿ ግን መብራት ማዳረስ ተስኗት፣ ወደ ፈረቃ ሥርዓት ገብታለች፤ የማንዴላ አገር ደቡብ አፍሪካ። ለምን?

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መብራት ኃይል 'ኢስኮም' ተብሎ ይጠራል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በኃይል አቅርቦት ስመ ገናና ነው። በዚህ ተቋም የተፈጠረው ቀውስ ግንቦት ላይ ምርጫ ለሚጠብቃቸው ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በመንበራቸው የመቆመር ያህል ነው። ሆኖም ምንም ማድረግ አልቻሉም።

ኢስኮም እስከ አፍንጫው ዕዳ ውስጥ ተነክሯል። ድርጅቱ ራሱ አፍ አውጥቶ 'ነገሮች ካልተሻሻሉ በታኅሣሥ ወር ቤሳቤስቲን ላይኖረኝ ይችላል' ብሏል።

ኢስኮም በዋናነት በማስተላለፊያዎች መጠነ ሰፊ ጥገና እያካሄድኩ ነው መብራት በፈረቃ ለማድረግ የተገደድኩት ቢልም ይህ ከፊል እውነት ብቻ ነው የሚሆነው።

ደቡብ አፍሪካ መብራት በፈረቃ ስታድል አሁን የመጀመርያዋ አይደለም። እንደ ጎርጎሮሲያውያኑ በ2008 እና በ2015 መብራት በፈረቃ ታድል እንደነበር።

አሁን በመብራት ኃይሉ ለተፈጠረው ቀውስ ሙስና፣ የሥልጣን መባለግ፣ የገቢ ማሽቆልቆል፣ የዕዳ መናር፣ የመሠረተ ልማት መፍረክረክ ሁሉም በእኩል ድርሻ አላቸው።

ኢስኮም መብራት የሚያመነጨው ሙሉ በሙሉ ከከሰል ነው። ከሰል በደቡብ አፍሪካ በሽበሽ ነው። ይህ ከከሰል ኤሌክትሪክን የማመንጨት ነገር በአፓርታይድ ዘመን ለአገሪቱ በበቂ ሁኔታ መብራት ያዳርስ ነበር። አሁን ግን ላሽቋል።

አንዱ ምክንያት ያን ጊዜ ጥቁሮች የሚኖሩባቸው ሰፈሮች መብራት አይቀርብላቸው ስለነበረ ነው። ሌላው ደግሞ በአጭር ዓመታት ውስጥ የኃይል ፍላጎት በእጥፍ ማደጉ ነው። ይህ ደግሞ የኢኮኖሚው መመንደግ ያመጣው 'በባርኮት ውስጥ ያለ መርገም' ነው።

ከዓመታት በፊት ይህ የኃይል አቅርቦት ችግር ሊከሰት እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ ሁለት አዳዲስ የኃይል ማመንጫ ግንባታ ተጀምሮ ነበር፤ ኩሲሊና ሜዱፒ የሚባሉ ፕሮጀክቶች።

እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች በ2015 ሥራ ይጀምራሉ ተብለው ነበር የተወጠኑት። ነገር ግን ግንባታቸው በግንባታ እቃዎች መናርና ለከት ባጣ የሙስና ቅሌት ተሽመድምዷል።

ባለፉት 10 ዓመታት ለደቡብ አፍሪካ መብራት ኃይል ከተሾሙ ስድስት ሥራ አስፈጻሚዎች በሪያን ሞሌፍ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር። ኾኖም ጸረ ሙስና ጠርጥሯቸዋል፤ የባለጸጎቹን የጉብታ ቤተሰብና የጃኮብ ዙማን ልጅ ለመጥቀም አሲረሃል በሚል።

ዛሬ ሀብታም የደቡብ አፍሪካ ሰፈሮች በታዳሽ ኃይል መብራት ቢያገኙም አብዛኞቹ ለመብራት ፈረቃ ተዳርገዋል።

መብራት ኃይል በበኩሉ 'እኔንስ ለምን አትረዱኝም፤ ፈረቃው ገቢዬ እንዲያሽቆለቁል አድርጎታል። በመብራት ታሪፍ ማሻሻያ ካልተደረገ በቁሜ መፍረሴ ነው' እያለ ነው። አሁን የመሥሪያ ቤቱ የዕዳ ቁልል እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ኢስኮም ደቡብ አፍሪካን መቀመቅ ሊከታት የሚችል የአገሪቱ ዋና ስጋት ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።