ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ባለሥልጣናት በአሲድ ጥቃት ግድያ ክስ ተመሠረተባቸው
የዩክሬን አቃቤ ሕግ ታዋቂ የፀረ-ሙስና ተሟጋችን በኢሰድ ጥቃት ለሞት ዳርገዋል ያላቸው ባለስልጣናት ላይ ክስ መሠረተ።
የ33 ዓመቷ ካትሪያና ሃንድዝዩክ ሕልፈት ዩክሬናውያንን እጅጉን ያስደነገጠ ነበር። የአሲድ ጥቃቱ ካደረሰባት ቃጠሎ በኋላ በሕክምና ስትረዳ ብትቆይም ከሦስት ወራት በፊት ሕይወቷ አልፏል። የፀረ-ሙሰና ተሟጋቿን ሕይወት ለማትረፍ ከ10 በላይ የቀዶ ሕክምና ተደርጎላት ነበር።
ክስ ከተመሠረተባቸው ባለሥልጣናት መካከል የአንድ ግዛት ምክር ቤት ኃላፊ ግድያውን በማቀነባበር ተጠያቂ ሆነዋል። ከእኚህ ግለሰብ በተጨማሪ ሌሎች 5 ሰዎች ከግድያው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ።
የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ ወደ 50 በሚጠጉ የፀረ-ሙስና አቀንቃኞች ላይ የተለያየ መልክ ያላቸው ጥቃቶች ተሰንዝረዋል።
ግድያውን በማቀነባበር የተከሰሱት ግለሰብ ቤት በፖሊስ የተበረበረ ሲሆን የተከሳሹ ጠበቃ ግን በደንበኛዬ ላይ የተገኘ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ይላሉ።
ክስ የተመሠረተባቸው የምክር ቤት ኃላፊም ሟቿን እንደማያውቋት እና ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው በመናገር ለምርመራው ተባባሪ መሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።