በካሊፎርኒያ ኪዊቦት የተባለችዋ ምግብ አመላላሽ ሮቦት በእሳት ተያያዘች

ምግብ አመላላሿ ሮቦት ሰዎች በፈጠሩት ስህተት በእሳት ተያይዛ መውደሟን የሮቦቷ ፈጣሪ አስታውቋል።

ኪዊቦት የተሰኙት ራሳቸውን የሚቆጣጠሩት ምግብ አመላላሽ ሮቦቶች ላለፉት 2 ዓመታት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በርክሌይ ግቢ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለተመጋቢዎች ምግብ በማመላለስ ስራ ተጠምደው ይውላሉ።

ያለፈው አርብ ግን ለአንዷ ሮቦት ጥሩ ዜና ይዞ አልመጣም፤ አገር ሰላም ብላ የታዘዘችውን ምግብ ለማድረስ ተፍ ተፍ ስትል ነበር የእሳት አደጋ የገጠማት፤ በእሳት ተያይዛ የመውደሟ መርዶም በማህበራዊ ሚዲያዎች ናኘ።

የሮቦቷ ሰሪ ኪዊ ለሮቦቷ እንደዚህ መሆን በስህተት የተገጠመባት ባትሪ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል።

ደርጅቱ በሰጠው መግለጫ በሮቦቷ ላይ የተገጠሙት ባትሪዎች መለያየት እንደጀመሩና ከዚያም ቀስ በቀስ እየተቀጣጠለ የእሳት ነበልባልና ጭስ እንደታየ ገልጿል።

"የግቢው ማህበረሰብ እሳቱን በፍጥነት ለመቆጣጠር በአቅራቢያ ያለውን የእሳት ማጥፊያ በመጠቀም ጥረት አድርገዋል" ሲሉ የነበረውን ሁኔታም አስረድተዋል።

ምንም እንኳን ሮቦቶች እንደዚህ ዓይነት አደጋ ሲያጋጥማቸው የመጀመሪያው ባይሆንም በእርሷ ላይ የደረሰው ግን ያልተጠበቀ ነበር።

በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት የአካባቢ ደህንነት ለመጠበቅ የምትንቀሳቀሰው ሮቦት 'ፋውንቴን' ውስጥ ወድቃ ሰጥማለች።

በዚህ ዓመት ታህሳስ ወርም አንዲት ሮቦት የአማዞን የልብስ መሸጫ ህንፃ ጋር ተጋጭታ እዚያ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ማስከተሏም ይታወሳል።

ኪዊ እንደዚህ አልፎ አልፎ ለሚፈጠሩ አደጋዎች ድጋሜ እንዳይከሰቱ መፍትሔ ለመዘየድ ሮቦቶቹን በሙሉ ከስራ ያገደ ሲሆን የታዘዙ ምግቦችን በሰው ማመላለስ እንደጀመረ አስታውቋል።

ድርጅቱ አክሎም እያንዳንዱ ሮቦቶች ላይ የሚገጠመውን ባትሪ የሚከታተል ሌላ ወስጠ-ስሪት (SoftWare) እንዳስገጠመ አስረድቷል።

ኪዊ ፌሊፕ ቻቬዝ በተባለ ግለሰብ የተቋቋመ ሲሆን እስካሁንም ሮቦቶቹን በመጠቀም 10 ሺህ የሚደርሱ ምግቦችን ለተጠቃሚዎች ማድረስ ችሏል።