ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያና ኤርትራ ጋር ባላቸው ግንኙነት ጥያቄ ቀረበባቸው
ከአንድ መቶ የሚደርሱ የሶማሊያ ፓርላማ አባላት በሃገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ላይ እምነት እንደሌላቸው የሚገልጽ የውሳኔ ሃሳብ አቀረቡ።
የፓርላማ አባላቱ ተቃውሟቸውን ያሰሙት ፕሬዝዳንቱ ከሕግ ውጪ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ተገቢ ያልሆነ ስምምነት አድርገዋል በሚል ነው።
ይህንንም ተከትሎ መቀመጫውን ሞቃዲሾ ያደረገው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት ላይ የፖለቲካ ውስጥ ውጥረት ተፈጥሯል።
የሶማሊያ ፓርላማ አፈጉባኤ የፓርላማ አባላቱ በፕሬዝዳንቱ ላይ ያቀረቡትን የውሳኔ ሃሳብ መቀበላቸውን አረጋግጠዋል።
በፕሬዝዳንቱ ላይ እምነት እንዳጡ የገለጹት የሶማሊያ የፓርላማ አባላት እንዳሉት ፕሬዝዳንት አብዱላሂ ፋርማጆ ከሃገሪቱ ሕገ መንግሥት ተቃርነው ከአካባቢው ሃገራት ጋር ስምምነት ፈጥረዋል በማለት ይከሷቸዋል።
በተጨማሪም ሶማሊያን ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር ለማዋሃድ ምስጢራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል ሲሉ ከሕግ ውጪ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የፓርላማ አባላቱ ፕሬዝዳት ፋርማጆ ላይ ክሳቸውን ካቀረቡ ከአንድ ቀን በኋላም ተቃዉሟቸውን አሰምተዋል። ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ የጠየቁት የፓርላማ አባላት እንዳሉት የሃገሪቱን ሉዓላዊነት በሚሸረሽር ሁኔታ ከሶማሊያ ወደቦች ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ኢኮኖሚያዊ ስምምነት እንዳደረጉ ከሰዋል።
አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉትም ይህ ውዝግብ የባሕረ ሰላጤው ሃገራት በሶማሊያ ውስጥ ካላቸው ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም የሶማሊያ ፖለቲከኞች በአካባቢው ተጽዕኗቸውን ለማጠናከር በሚፎካከሩት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ከኳታር አንጻር ባለ መከፋፈል ነው።
የሶማሊያ ፖለቲከኞች ድጋፍ ከሚሰጧቸው ሃብታም የባሕረ ሰላጤው ሃገራት ጎን የቆሙ ሲሆን ይህ ውዝግብ ደግሞ በሃገሪቱ ተጨማሪ ያለመረጋጋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል።
ይህን የፓርላማ አባላትን ጥያቄ በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦች እየተነሱ ሲሆን ጉዳዩ ለፓርላማው ውይይትና ውሳኔ ይቀርብ እነደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሃገራቱ መካከል የነበረውን የጠላትነት ስሜት ችላ በማለት ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎች ወዳጅነታቸውን በማጠናከር ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል።
ቀደም ያሉት የሶማሊያ አስተዳደሮች በፕሬዝዳንቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩና በፐፕሬዝዳንቱ መካከል በሚፈጠሩ ያለመግባባቶች ሳቢያ ሲናጡ የቆዩ ቢሆኑም አብዱላሂ ፋርማጆ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ግን ሶማሊያ ፖለቲካዊ መረጋጋትን አግኝታ ቆይታለች።