የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ41 ዓመታት በኋላ ወደ ሶማሊያ በረራ ጀመረ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ41 ዓመታት በኋላ ወደ ሶማሊያ በረራ አድርጎ በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ አረፈ።

በቦይንግ 737 የተደረገው በረራ የተመራው በሴት አውሮፕላን አብራሪ ሲሆን፤ 50 ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።

አውሮፕላኑ ሞቃዲሾ የደረሰው ከአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ሁለት ሰአት ገደማ ከበረረ በኋላ ነበር። ከተሳፋሪዎቹ መካከል በኢትዮጵያ የሶማሊያ ኤምባሲ ፈርስት ካውንስለር አቶ አብዱላሂ መሀመድ ዋርፋ ይገኙበታል።

አቶ አብዱላሂ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በረራው መጀመሩ የሁለቱን ሀገሮች የንግድ ግንኙነት ያጠናክራል።

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ሲነሳ፣ በበረራው እኩሌታ እንዲሁም ሞቃዲሾ ካረፈ በኋላ ልዩ ልዩ መሰናዶዎች ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሶማሊያ በረራ ማድረግ ያቋረጠው እንደ አውሮፓውያኑ በ1970ዎቹ በሁለቱ ሀገሮች የድንበር ግጭት ከተከሰተ በኋላ ነበር።

በአሁን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሶማሊያው ፕሬዘዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆና ከኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ይገኛሉ።