ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር አሲረዋል የተባሉ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
የፈረንሳይ ባለስልጣናት በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲያሴሩ ነበር ያሏቸውን ስድስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታወቁ።
ማንነታቸው ያልተገለጸው 5 ወንዶች እና አንዲት ሴት በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ፈረንሳይ መሆኑን ባለስልጣናቱ ጨምረው ገልጸዋል።
ለፍርድ ቤት ቅርብ የሆኑ ምንጮች ''ወንጀለኛ የሽብር ቡድን ማሕበር'' የሚል ምረመራ ተጀምሮባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ማንነትም ሆነ ያሴሩት ሴራ ዝርዝር ለህዝብ ይፋ አልሆነም።
ተጠርጣሪዎቹ ረዘም ላለ ጊዜ በፈረንሳይ መንግሥት የቅርብ ክትትል ይደረግባቸው እንደነበረ የሃገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ አስታውቋል።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ምስራቅ ፈረንሳይ ውስጥ የ1ኛ የዓለም ጦርነት የውጊያ ስፍራዎችን እየጎበኙ ሳለ ነው ይህ ዜና የተሰማው።
በተመሳሳይ መልኩ ከአንድ ዓመት በፊት የ23 ዓመት ወጣት ፕሬዚዳንት ማክሮንን ለመግደል አሲረሃል ተብሎ በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።