በብሪደርስ ዋንጫ ሰክሮ ፈረስ ሲጋልብ የነበረው ተወዳደሪ ታሰረ

ጉዳዩ ጠጥተው አያሽከርክሩ ብቻ ሳይሆን ጠጥተው አይጋልቡም ያስባለ ነው።

ኬንተኪ ውስጥ በርካታ ተመልካች በተገኘበት በተካሄደው የብሪደርስ ዋንጫ፤ የፈረስ ግልቢያ ውድድር ላይ ጠጥቶ ሲጋልብ የነበረ ግለሰብ ለእስር ተዳርጓል።

የኬንተኪ ፖሊስ እንዳስታወቀው የ24 ዓመቱ ማይክል ዌልስ - ሮዲ በውድድሩ ላይ በተከለከለ የመጋለቢያ መስመር ውጪ ሳይቀር ሲጋልብ ነበረ።

"ግለሰቡ በስካር ጥምብዝ ከማለቱ የተነሳ አካባቢውን በጩኀት ያናውጠው ነበር፤ የሚነገረውንም ትዕዛዝ አይፈፅምም፤ እንዲቆም ቢነገረውም አሻፈረኝ ብሏል" ሲል ፖሊስ ጨምሮ ተናግሯል።

ዌልስ ሮዲይ ክስ የተመሰረተበት ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ አልኮል በመጠጣትና ያልተገባ ድርጊት በመፈፀም ሲሆን ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

ውድድሩን በአሸናፊነት የሚያያጠናቅቅ 6 ሚሊዮን ዶላርና የዋንጫ ሽልማት ተዘጋጅቶ ነበር፤ በውድድሩ ፈጣን ጋላቢው ጆል ሮሳሪ ሊያሸንፍ ችሏል።

ብሪደርስ ዋንጫ በአሜሪካ በርካታ ተመልካቾች የሚታደሙት ደማቅ ውድድር ነው።