ፈረንሳያዊው አርፋጅ ተማሪ መምህሩ ላይ የመጫወቻ ሽጉጥ በመደቀኑ ተከሰሰ

ፈረንሳዊው ተማሪ መምህሩ ላይ ሽጉጥ ሲደቅን የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ከታየ በኋላ በከፋ ጠብ አጫሪነት ተከሷል።

ተማሪው በወንበሯ ላይ የተቀመጠችው መምህርት ላይ የፕላስቲክ መጫወቻ ሽጉጥ ደቅኖ ቀሪ እንዳታደርገው እየጮሀ ሲናገር በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ይታያል።

ድርጊቱ አብረውት በሚማሩ የክፍል ጓደኞቹ ተቀርጾ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ የተለቀቀው ሐሙስ ዕለት ነበር።

መምህርቷ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ለተማሪዎቹ እያስረዳች ላፕ ቶፑዋ ላይ ስትሰራ ትታያለች።

ተማሪው አርፍዶ በመምጣቱ ምክንያት ቀሪ በመደረጉ መበሳጨቱን በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ ዘግቧል።

የ15 ዓመቱ ተማሪ ድርጊቱን "ለቀልድ ነው" ብሎ ያስተባበለ ሲሆን እየተቀረፀ መሆኑንም እንዳላወቀ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

መምህርቷ አርብ ዕለት ወደ ፖሊስ ዘንድ ሄዳ አቤቱታዋን አቅርባለች።

ተማሪውም ወላጅ አባቱን በመያዝ የዚኑ ዕለት ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ሄዶ እጁን ሰጥቷል።

ድርጊቱ በፕሬዝዳንት ማርኮንና በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተኮነነ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከሰትን አመፅ ለመከላከል የሚያስችል ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

በትምህርት ቤቱ ላለፉት 25 ዓመታት እንደሰሩ የተናገሩ አንድ መምህር ሌሞንድ ለተሰኘ ጋዜጣ እንደተናገሩት "እንዲህ አይነት ድርጊት አልተለመደም" ካሉ በኋላ ተማሪዎቹ "የተግባቦት ክህሎትና ግብረገብ" እንደሚማሩ ተናግረዋል።