ፖሊስ: አብዲ ሞሐመድ ዑመር ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤት ተናገረ።

አቶ አብዲ ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀጠሯቸው መሰረት በቀረቡበት ወቅት ፖሊስ የታሰሩበትን ቢሮ መስታወት በመስበርና የጥበቃ አባልን በማነቅ ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል ሲል ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

አቶ አብዲ በበኩላቸው ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ እና ሆን ተብሎ ስማቸውን ለማጥፋት የተደረገ ሴራ ነው ብለዋል።

አቶ አብዲ ጨምረውም ምቹ ባልሆነ እስር ቤት መታሰራቸውን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነ ታራሚ የታሰሩበትን ክፍል በር ገንጥሎ በመግባት ሁለት ቀን ጉዳት ሊያደርስባቸው እንደሞከረና ይህም በደህንነቴ ላይ ስጋት ፈጥሮብኛል በማለት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱ ኢቲቪ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ፖሊስ በአቶ አብዲ መሐመድ የክስ መዝገብ ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ፖሊስ የምርመራውን ውጤት ለጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ይዞ እንዲቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።