የቪንሰንት ኮምፓኒ ወላጅ አባት የመጀመሪያው ጥቁር ከንቲባ ሆነው ተመረጡ

የማንችስተር ሲቲ እና የቤልጄም ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ቪንሰንት ኮምፓኒ ወላጅ አባት በቤልጂየም የመጀመሪያው ጥቁር ከንቲባ በመሆን ተመረጡ።

ፒየር ቪንሰንት ብራስልስ ውስጥ በምትገኝ ጋንሾሬን በምትባል ምርጫ ጣቢያ ላይ በርካታ ድምጽ በማግኘታቸው ከንቲባ ለመባል በቅተዋል።

ኮምፓኒ እአአ በ1975 ነበር ከዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ወደ ቤልጄም የመጡት።

ሰውዬው ከ2006 ጀምሮ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ በብራሰልስ ግዛት ውስጥ የህዝብ ተወካይ በመሆን ከአራት ዓመታት በፊት የምክር ቤት ወንበር ማሸነፍ ችለው ነበር።

የማንችስትር ሲቲ እግር ኳሰኛ በሆነው ዝነኛው ልጃቸው በርካቶች ያውቋቸዋል። የቪንሰንት ኮምፓኒ ወንድም ፍራንኮኢስ ደግሞ ቤልጄም ውስጥ ለሚገኝ ክለብ ይጫወታል።

ወንድማማቾቹ ወላጅ አባታቸውን በጋራ በመሆን የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በቪንሰንት ኮምፓኒ ኢንስታግራም ገጽ ላይ የተለጠፈው የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት፤ ወንድማማቾቹ ''ታሪክ ተሰራ! አባታችን በጣም ኮርተንብሃል'' ይላል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትውልዳቸው ከቤልጄም ውጪ የሆኑ ስደተኞች በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል። የቱርክ ስደተኞች ልጅ የሆነው ኢሚር ኪር 2012 ላይ የሴንት-ጆስ ከንቲባ በመሆን ተመርጦ ነበር። ወላጅ አባቷ ከሞሮኮ የሆኑት ናዲያ ሳሚኔት ደግሞ የሎንደርዘል መሪ በመሆን 2016 ላይ ተመርጣ ነበር።