የቪንሰንት ኮምፓኒ ወላጅ አባት የመጀመሪያው ጥቁር ከንቲባ ሆነው ተመረጡ

ፒዬር ቪንሰንት ኮምፓኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማንችስተር ሲቲ እና የቤልጄም ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ቪንሰንት ኮምፓኒ ወላጅ አባት በቤልጂየም የመጀመሪያው ጥቁር ከንቲባ በመሆን ተመረጡ።

ፒየር ቪንሰንት ብራስልስ ውስጥ በምትገኝ ጋንሾሬን በምትባል ምርጫ ጣቢያ ላይ በርካታ ድምጽ በማግኘታቸው ከንቲባ ለመባል በቅተዋል።

ኮምፓኒ እአአ በ1975 ነበር ከዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ወደ ቤልጄም የመጡት።

ሰውዬው ከ2006 ጀምሮ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ በብራሰልስ ግዛት ውስጥ የህዝብ ተወካይ በመሆን ከአራት ዓመታት በፊት የምክር ቤት ወንበር ማሸነፍ ችለው ነበር።

የማንችስትር ሲቲ እግር ኳሰኛ በሆነው ዝነኛው ልጃቸው በርካቶች ያውቋቸዋል። የቪንሰንት ኮምፓኒ ወንድም ፍራንኮኢስ ደግሞ ቤልጄም ውስጥ ለሚገኝ ክለብ ይጫወታል።

ወንድማማቾቹ ወላጅ አባታቸውን በጋራ በመሆን የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የ Instagram ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን Instagram ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ Instagram ይዘት መጨረሻ

በቪንሰንት ኮምፓኒ ኢንስታግራም ገጽ ላይ የተለጠፈው የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት፤ ወንድማማቾቹ ''ታሪክ ተሰራ! አባታችን በጣም ኮርተንብሃል'' ይላል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትውልዳቸው ከቤልጄም ውጪ የሆኑ ስደተኞች በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እየጨመረ መጥቷል። የቱርክ ስደተኞች ልጅ የሆነው ኢሚር ኪር 2012 ላይ የሴንት-ጆስ ከንቲባ በመሆን ተመርጦ ነበር። ወላጅ አባቷ ከሞሮኮ የሆኑት ናዲያ ሳሚኔት ደግሞ የሎንደርዘል መሪ በመሆን 2016 ላይ ተመርጣ ነበር።