አፍሪካዊያን ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትን መጎብኘት ለምን ይከብዳቸዋል?

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, aviation-images.com

ናይጄሪያዊው ቁጥር አንድ የአፍሪካ ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ በአህጉሪቱ ውስጥ ወደ ሚገኙ ሃገራት ለመጓዝ የ38 ሃገራት ቪዛ ግድ ይለኛል ብለው ነበር። አብዛኛው የአውሮፓ ሃገራት ዜጎች ግን ወደ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ያለ ቪዛ መጓዝ ይችላሉ።

እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት የአፍሪካ ህብረት የአባል ሃገራት ዜጎች ወደ አፍሪካ ሃገራት ጉዞ ሲያደርጉ ይጠየቁ የነበረውን ቪዛ ለማስቀረት ዕቅድ ነበረው።

ከ5 ዓመታት በፊት የተደረሰው ስምምነት በቀጣዮቹ 50 ዓመታት ውስጥ ለማሳካት ከተሰበው ራዕይ እና ፍኖተ ካርታ መካከል ዋነኛው ነበር።

እስካሁን ግን በምስራቅ አፍሪካ በህንድ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘዋ አፍሪካዊት ሃገር ሲሼልስ ብቻ ናት ሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ያለ ቪዛ ሊጎበኟት የሚችሉት።

በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ አፍሪካዊያን ያለ ቪዛ ሊጓዙ የሚችሉት 22 በመቶ ወደሚሆኑ የአፍሪካ ሃገራት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያውያን ደግሞ ያለ ቪዛ ወይም በመዳረሻ ቪዛ ሊጎበኟቸው የሚችሏቸው ሃገራት ኬንያ፣ ሲሼልስ፣ ዩጋንዳ፣ ቶጎ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሪታኒያ፣ ማደጋስካር፣ ጊኒ ቢሳሁ፣ ጂቡቲ፣ ኮሞሮስ፣ ኬፕ ቨርድ እና ቡሩንዲ ናቸው።

የአፍሪካ ህብረት ልክ እንደ የአውሮፓ ህብረት ሃገራት ሁሉ ድንበር አልባ አፍሪካዊ አሃጉር በመፍጠረ 1.2 ቢሊዮን ህዝብ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ይህን እቅድ ለማሳካት በርካታ ውጣውረዶች ተጋርጠውበታል።

55 የአፍሪካ ሃገራትን የጎበኘው ደቡብ አፍሪካዊው ጦማሪ ኬቺ ናዝማ ''መሪዎቻችን በቀኝ ግዛት ተሰምሮ የተሰጣቸውን ድንበር ላለማስደፈር ብዙ ርቀት ይጓዛሉ'' ሲል የአፍሪካን መሪዎች ይተቻል።

ከአፍሪካ ሃገራት እንደ ደቡብ አፍሪካ ሌሎች አፍሪካውያን ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ የሚከለክል፤ እንዲሁም ለተቀረው ዓለም በሩንን የሚክፈት የለም።

28 የአውሮፓ ሃገራት ዜጎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ያለ ቪዛ መጓዝ ይችላሉ። ደቡብ አፍሪካ ለ15 አፍሪካውያን ሃገራት ብቻ ነው በሯን ክፍት ያደረገችው።

የአፍሪካውያን ፓስፖርት

ናሚቢያ፣ ሞሪሺየስ፣ ጋና፣ ሩዋንዳ፣ ቤኒን፣ ኬንያ እና እንዲሁም ኢትዮጵያ በቅርቡ ሌሎች አፍሪካውያን ዜጎች ወደ ሃገሮቻቸው እንዲገቡ የጉዞ መስፈርቶችን ቀንሰዋል።

የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ሃገራትን ፓስፖርት የሚተካ ''አፍሪካን ፓስፖርት'' (የአፍሪካውያን ፓስፖርት) በተሰኝ አዲስ ፓስፖርት እ.አ.አ. በ2016 ለመቀየር እቅድ ነበረው። እቅዱ ባይሳካም የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ኢድሪስ ዴይባ የፓስፖርቱ ባለቤት ለመሆን ችለዋል።

የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ኢድሪስ ዴይባ እ.አ.አ. 2016 ላይ የፓስፖርቱ ባለቤት ለመሆን ችለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/BBC

የምስሉ መግለጫ, የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ኢድሪስ ዴይባ እ.አ.አ. 2016 ላይ የፓስፖርቱ ባለቤት ለመሆን ችለዋል።

ጉዞወጪ መናር

አፍሪካዊያን ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትን እንዳይጎበኙ ተግዳሮት የሚሆንባቸው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በቂ የመንገደኞች የበረራ አገልግሎቶተች አለመኖራቸው ነው። ቢገኙም ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም።

በዚህ ላይ ደግሞ በየመዳረሻቸው ለቪዛ የተጋነነ ዋጋ ይጠየቃሉ።

ጅቡቲ ለአንድ ሰው ቪዛ 90 ዶላር ትጠይቃለች። የሸንገን ቪዛ ለማግኘት ግን ሚከፈለው 75 ዶላር ብቻ ሲሆን፤ 26 አውሮፓ ሃገራትን መጎብኘትም ያስችላል።