የላምፔዱሳው ኤርትራውያን እልቂት አምስተኛ ዓመት ተዘከረ

እአአ ጥቅምት 3፣ 2013 ላይ አብዛኞቹ ኤርትራውያን የሆኑ ስደተኞችን ጭና ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ስትጓዝ የነበረች መርከብ በላምፔዱሳ ደጃፍ ስትደርስ ሰጠመች። ከዚያን ዕለት ጀምሮ ኤርትራውያን ቀኑን በሀዘን ይዘክሩታል።

ብዙ ስደተኞች ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚያደርጉት ጉዞ ብዙ አደጋ ያጋጥማቸዋል፤ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ የታየበት እና በዓለም መገናኛ ብዙሃን የተሰማ አደጋ ግን እምብዛም ነው።

አምስት መቶ ስደተኞችን ጭና ከሊቢያ ባህር ዳርቻ የተነሳችው መርከብ ከ 25 ሰዓታት በላይ ያለ አንዳች ችግር ስትጓዝ ነበር። ላምፔዱሳ ደሴት ለመድረስ አንድ ኪሎሜትር ብቻ ሲቀራት ባልታወቀ ምክንያት ባጋጠማት ቃጠሎ የብዙ ኤርትራውያን ሕይወት ተቀጭቷል።

በተለያዩ የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች፤ ጨቅላ ህፃናትን የታቀፉ እናቶች፣ ዝምድና ያላቸው እና የአንድ አካባቢ ልጆች ጉዟቸውን በሰላም ለመጨረስ ለፈጣሪያቸው እየፀለዩ እና እየተሳሳቁ በሚጓዙበት ወቅት በቅፅበት ሁኔታዎች ተለወጡ።

በዚያች መርከብ ውስጥ የነበረ እና በሕይወት የተረፈው አድሓኖም ሰመረ ስለዛች 'ጥቁር ቀን' ያስታውሳል።

''የመርከቧ ካፒቴን 'ከዚህ በኋላ መሄድ ስለማንችል፤ እዚህ ሆነን እርዳታ መጠየቅ አለብን' በማለት ምልክት ለመስጠት አንሶላ አቃጠለ፤ እናም የመርከቧ ተጓዦች በድንጋጤ ለማምለጥ ሞከሩ፤ ከዚያም መርከቧ ሚዛኗን ስለሳተች አደጋው አጋጠመ'' በማለት ይናገራል።

መርከቧ ገና ከሊቢያ ስትነሳ ጀምሮ ከልክ በላይ ብዙ ሰዎችን ጭና እንደነበር አድሓኖም ያስታውሳል።

ከሌሊቱ 10 ሰዓት አደጋው ሲያጋጥም የነበረው ሁኔታ ምንም ግዜ ከዓዕምሮው የማይጠፋ መጥፎ ትውስታ እንደሆነ ይገልፃል።

''መርከቧ ወደ ቀኝ ከተገለበጠች በኋላ፤ አንድ ሰዓት ለሚሆን ጊዜ፤ ወደ መርከቧ ለመውጣት ስንሞክር መልሳ ትገለብጠናለች፤ ለአንድ ሰዓታት ያህል ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገናል ግን አልሆነም፤ መርከቧ ሁላችንንም ይዛ ሰጠመች'' ይላል።

'እርዱን!' የሚለው ድምፅ እና ጩኸት በህይወት እስካለ ድረስ ለዘልዓለም ከዓዕምሮው የማይጠፋ እንደሆነ አድሓኖም ይናገራል።

"እባካቹን ለቤተሰቦቼ ንገሩልኝ! መዋኘት አልችልም፤ ለቤተሰቦቼ ብቸኛ ነኝ የሚሉ ንግግሮች መቼም ቢሆን ከዓዕምሮዬ አይጠፋም፤ አስታውሳለሁ ሄለን የምትባል እናት 'ወይኔ ልጆቼ..........!' ስትል እስከአሁን ድረስ ድምፅዋ በጆሮዬ ያቃጭላል። 'ልጆቼ!.... ኧረ ልጆቼ!....' የሚሉ የሚረብሹ ድምፆችን መቼም ቢሆን አልረሳቸውም'' ይላል።

በዚህ አደጋ ወንድሙን ያጣው የስዊድኑ ነዋሪ አቶ አዳል ንጉሰ በበኩሉ ገና በማለዳው ስለአደጋው የሰማው ከቢቢሲ ራድዮ ነበር።

ከሁለት ቀን ቀደም ብሎ ሊቢያ የነበረው ወንድሙ ጉዞ ለመጀመር እንደተዘጋጁ ስለነገረው፤ በዚያችው መርከብ ሊኖር ይችላል በሚል እንደደነገጠ ይናገራል።

''ሊቢያ ደውየ ከአንድ ቀን በፊት ተጉዟል ባሉኝ ግዜ፤ ወንድሜ እዚያች መርከብ ላይ እንደሆነ ገባኝ'' በማለት ስለ ሁኔታው ያስረዳል።

'በሕይወት ያገናኙኝ ካልሆነም መርዶዬን ይንገሩኝ' በማለት የወንድሙን ፎቶ ይዞ ወደ ላምፔዱሳ አቀና።

ሳይውል ሳያድር ወደ ላምፔዱሳ ያቀናው አዳል ንጉሰ ከአደጋው የተረፉትን ሰዎች አግኝቶ "ይህን ሰው ታውቁታላችሁ?" በማለት የወንድሙን ፎቶ እያሳየ መወትወት ጀመረ።

በሚጠይቃቸው ሰዎች ፊት ሀዘን ቢነበብም ጭንቅላታቸውን ወደ ግራ እና ቀኝ በመወዝወዝ አናውቀውም በማለት እንደነገሩት ያስታውሳል።

በኋላ ላይ ግን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) የወንድሙን ፎቶ ይዞ በመሄድ እንዲፈልጉለት ተስፋ ባለመቁረጥ ተማፀናቸው።

ይሁን እንጂ በመጨረሻም "ወንድምህ በዚህች መርከብ ነበር፤ በህይወት መትረፍ ግን አልቻለም" የሚለውን መራር መርዶ ነገሩት፤ተስፋውም ጨለመ።

በወርሃ ጥቅምት 2013 ያጧቸውን ውዶቻቸውን ለማስታወስ ዘመድ አዝማድ ተሰባስበው ቀኑን ይዘክሩታል።

አድሓኖምም እነዚያን 'እየመጣን ነው፤ ገብተናል' እያሉ የተለዩትን፣ በሰሀራ በርሃ አብረውት የተጓዙትን፣ በሊቢያ የችግሩ ተካፋዮች የነበሩትን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚያ በሞት አፋፍ ላይ ሆነው 'እኔ ለቤተሰቦቼ አንድ ነኝ. . .፣ . . . ለቤተሰቦቼ ንገሩልኝ፣ . . . እባካችሁ እየሞትኩኝ ነው፣ ወይኔ ልጆቼ!....' በማለት ሲጮኹ የነበሩትንና በአጭር የቀሩትን መንገደኞች ለማስታወስ ወደ ላምፔዱሳ ተጉዟል።

"ከከተማዋ ከንቲባ ጋር በመገናኘት ከአሁን በፊት የተከልናቸውን 368 ችግኞች ኮትኩተናል፤ ከዚህ በተጨማሪ ችግኞቹ በሚገኙበት ቦታ ሐውልት እንድንሰራ ፈቃድ ጠይቀናል'' በማለት የአውሮፓ በር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ፀሎት እንደሚያደርሱ እና አደጋው ወዳጋጠመበት ቦታ በአምስት መርከቦች በመሄድ የአበባ ጉንጉን እንደሚያስቀምጡ ነገሮናል።