ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲስ አበባ ውስጥ በፖሊሶች መካከል በነበረ የተኩስ ልውውጥ ሕይወት ጠፋ
አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመኖሪያ ህንፃ አካባቢ ትናንት ሌሊት በነበረ የተኩስ ልውውጥ የሰው ህይወት መጥፋቱን የዓይን እማኞች ገለፁ።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህንፃ ጥበቃ ከተሰማሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል የተደረገ እንደሆነ በተነገረው የተኩስ ልውውጥ ሶስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
የተኩስ ልውውጡ እኩለ ሌሊት አካባቢ ተጀምሮ እስከ ንጋት መቀጠሉን በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ጨምረው ገልፀዋል።
ተኩሱን የጀመረው በጥበቃ ላይ ከነበሩት የፖሊስ አባላት መካከል አንዱ እንደሆነና በምላሹም ሌሎች አባላት ተኩስ በከፈተው አባል ላይ የተኩስ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ተኩሱን የጀመረው የፖሊስ አባል ወደ 9ኛ ፎቅ በመውጣት በሌሎች አባላቶቹ ላይ ተኩስ መክፈቱን የዓይን ዕማኞች ተናግረዋል።
በተኩስ ልውውጡ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችና የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው በአካባቢው የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆናቸው ሲነገር፤ ጥቃቱን የጀመረው አባልም መገደሉ ታውቋል።
ጥቃቱን የከፈተው አባል ለምን ድርጊቱን እንደፈፀመ ምክንያቱ ያልታወቀ ሲሆን ከአለቆቹ ወይም ከባልደረቦቹ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ጥቃቱ በተፈፀመበት ህንፃና በአካባቢው ባሉ መኖሪያዎች የሚገኙ ሰዎች ለሰዓታት በነበረው የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ ሌሊቱን በስጋት ማሳለፋቸውን ገልፀዋል።
በህንፃው አካባቢ ያለው ዋነኛ መንገድም ለረጅም ሰዓታት ተዘግቶ እንደነበር ተገልጿል።
ስለ ክስተቱ ከፌደራል ፖሊስ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሰከረ የፌደራል ፖሊስ ኦፊሰር ሁለት የስራ ባልደረቦቹን ተኩሶ እንደገደለና ጥቃት አድራሹም ሕይወቱ እንዳለፈ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማልን ጠቅሰው ዘግበዋል።