ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጉባኤው ብአዴንን የት ያደርሰዋል?
በገዢው ግንባር ኢህአዴግ ጥምረት ውስጥ በተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና አላቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤውን ያካሂዳል።
የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ሆኖ በቆየባቸው ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በውስጡ አንዳንድ ለውጦችን እያደረገ በገዢው ግንባር አባልነት ዘልቋል።
የብአዴን መስራች አባላት ዋነኛ መሠረታቸው ከሆነው ኢህአፓ በመለየት መንቀሳቀስ በጀመሩበት ጊዜ መጠሪያቸውን ኢህዴን (የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) የሚል አድርገው ነበር።
ነገር ግን በገዢው ግንባር ውስጥ ያሉት ሦስት ድርጅቶች የተወሰነ ሕዝብና አካባቢን የሚወክል መጠሪያ በመያዛቸው ኢህዴን በተለይ የአማራ ህዝብን ወካይ የኢህአዴግ አባል መሆኑን ለማጉላት ስያሜውን ወደ ብአዴን ቀይረ።
ከዚህ ውጪ ግን እንደቀሪዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በግንባሩ ስር በመሆን ተመሳሳይ ለውጦችንና ውሳኔዎችን በክልሉ ውስጥ ሲወስንና ሲያስፈፅም ቆይቷል።
በዚህም በርካቶች ብአዴን የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ አቋም የሌለው እንዲሁም መጠሪያው ያደረገውን ህዝብ ጥቅምና መብት ማስከበር የማይችል ድርጅት ነው በማለት ሲተቹት ቆይቷል።
በተለይ ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖሩ አማሮች የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሟቸው ብአዴን አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን የሚጠበቅበትን አልተወጣም የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ለረዥም ጊዜ የተለያዩ አካላት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ላይ ያሉት ግለሰቦች ከአማራ ህዝብ አብራክ የወጡ ባለመሆናቸው በአግባቡ ሊወክሉት አይችሉም በማለት ከንቅናቄው እንዲወጡ በተለያየ መንገድ ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።
ግለሰቦቹ የወከሉትን ህዝብ በአግባቡ አላገለገሉም ከመባላቸው ባሻገር የድርጅቱንና የህዝብን ንብረት አባክነዋል፤ እንዲሁም እንደቤተሰብ ንብረት ተገልግለውባቸዋል የሚሉ ወቀሳዎችም ሲቀርቡባቸው ነበር።
በዚህም ሳቢያ በተለያዩ ስፍራዎች ወቀሳና ተቃውሞዎች ሲቀርቡበት የቆየው ብአዴን ንቁ ሆኖ በኢህአዴግ ውስጥ በመንቀሳቀስ የህዝቡንና የክልሉን ጥቅም የሚያስከብሩ ሥራዎችን እንዲሰራ ከውስጥም ከውጪም ግፊቶች ሲደረጉበት ቆይቷል።
በተለይ ከ2008 ወዲህ በተለያዩ የሃገሪቱና የክልሉ አካባቢዎች እየተጠናከረ የመጣው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ንቅናቄውን ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግን ጭምር ስጋት ውስጥ በማስገባቱ በግንባሩ ውስጥ ለውጦችን ለማድረግ ሰፊና ተከታታይ ስብሰባዎች ተካሂደው ነበር።
በግንባሩና በመንግሥት አመራር ላይ ለውጦችን ይዞ የመጣው ተከታታይ ስብሰባና ግምገማ በኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ ውስጥም ከፍተኛ የሚባል፣ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥና መነቃቃትን በመፍጠሩ በርካቶች ብአዴንም ይህንን ለውጥ በማጠናከር በኩል አስተዋጽኦ እንደነበረው ይናገራሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በነሐሴ ወር አጋማሽ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳን በጥረት ኮርፖሬት ላይ በፈጠሩት ችግር ምክንያት እስከ ድርጅቱ ጉባኤ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ታግደው እንዲቆዩ ውሳኔ አሳልፏል።
ከዚህ ውሳኔ በኋላ የታገዱት አባላት ከንቅናቄው አመራሮች ጋር በመገናኛ ብዙሃን እሰጥ አገባ ገጥመው ነበር።
የአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤም በአቶ በረከትና በአቶ ታደሰ ላይ የመጨረሻ ውሳኔውን ከማሳለፍ ባሻገር ሌሎች መስራችና ነባር አባላቱን እንደሚያሰናብት እየተነገረ ነው።
ግልጽ ያልሆነው ነገር እነዚህ የሚሰናበቱት አመራሮች ኦዴፓ (ኦህዴድ) እንዳደረገው በክብር ይሰናበቱ ይሆን የሚለው ነው።
የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ለረጅም ጊዜ ሲተቹበት የቆየው አዳዲስና ወጣት አመራሮችን አለማብቃታቸው ዋነኛው ሲሆን በድርጅቱ ውስጥ ያልተጠበቁ ለውጦችን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ እንዳመጡ የሚነገርላቸው ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ወጣቶችን ወደ አመራር የማምጣቱ ጥያቄ በየአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።
በዚህም ኦዴፓ እንዳደረገው ብአዴንም በርካታ ቀደምት የድርጅቱን አመራሮች በማሰናበት አዳዲስ ወጣቶችን ወደፊት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም የበርካታ የክልሉን ወጣቶች ቀልብ እየሳበ ያለውን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ተግዳሮት ለመቋቋም ሊጠቀምበት ይችላል።
ብአዴን "የለውጡ ቀጣይነት ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዲሞክራሲያዊ አንድነት " በሚል መሪ ሀሳብ የሚያካሂደው 12ኛ ደርጅታዊ ጉባኤ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም በተለያዩ መስኮች የለውጥ እርምጃዎችን በመውሰድ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ተመራጭ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ መገኘት የሚያስችሉትን ውሳኔዎች እንደሚሰጥበት ንቅናቄው በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም የብአዴን አቻ ኦህዴድ እንዳደረገውና የንቅናቄው አባላት ጥያቄ እንደሆነ የተነገረው የድርጅቱን ስያሜ ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይም ማሻሻያ እንደሚያደረግ ይጠበቃል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ባለፉት ዓመታት የአማራ ክልልን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ ለህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ለመፍታት የሚረዱ መንገዶች ላይ ውይይት እንደሚያደርግም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በድርጅቱ ስር ያሉ የልማት ድርጅቶች፣ ማለትም ጥረት ኮርፖሬት እና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ የተባሉት ድርጅቶች ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግሥት እንዲሆን ተወስኗል።