አቶ በረከት ስምኦን ከብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታገዱ

የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አቶ በረከት ስምኦንን እና አቶ ታደሰ ካሳን ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ማገዱን ይፋ አደረገ።

የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ጉባኤ ላይ የነበረ ሲሆን፤ ጉባኤው ሲጠናቀቅ አቶ በረከትን እንዲሁም አቶ ታደሰን ማገዱን አስታውቋል።

ኮሚቴው የሁለቱን አባላት እገዳ ባስተላለፈበት ጉባኤ ሌሎችም አዳዲስ ውሳኔዎች ላይ መደረሱን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

የአቶ በረከት የአቶ ታደሰ እገዳ "በጥረት ኮርፖሬት ላይ ከሰሩት ጥፋት ጋር የተያያዘ ነው" ተብሏል። ስለዚህም እስከ ቀጣዩ የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ጉባኤ ድረስ ከኮሚቴው አባልነት መታገዳቸው ታውቋል።

በጉባኤው ላይ ከተላለፉ ውሳኔዎች መካከል፤ ነባር አመራሮች በማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው መመሪያ መሻሩ ይገኝበታል።