ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህንዳውያን ታዳጊዎች ኤቨረስት ተራራ ላይ ሰንደቅ ዓላማ አውለበለቡ
ከህንድ ገጠራማ ስፍራ የመጡ አምስት ታዳጊዎች ባለፈው ግንቦት ወር የኤቨረስት ተራራን በመውጣት ስማቸውን በታሪክ መዝገብ ማስቀመጥ እንደቻሉ የ10 ወር ጉዟቸውን የተከታተለ አንድ ሪፖርት አስታውቋል።
በአውሮፓውያኑ ግንቦት ወር በኤቨረስት ተራራ አናት ላይ ሰንደቅ ዓላማውን የሰቀለችው የ18 ዓመቷ ታዳጊ ማኒሻ ዲሁርቬ "ጥረቴ ተሳክቶ ለማየት አሁንም ብርታት ነው የሚሰማኝ " ብላለች።
አሁን ባለችበት መንፈስ ወደኋላ ዞር ብላ ስታስበው ጭራሽ የማይሞከር መስሏት ነበር።
ነገር ግን ልክ ተራራውን ወጥታ እንዳጠናቀቀች በአይኗ ይታይ የነበረው የብርሃን ፀዳል ደስታዋን አሳብቋል።
"ከተራራው ጫፍ ላይ ሆኜ ወላጆቼን ፣ ዘመዶቼን፣ መንደሬን፣ ቤቴን ፣ ጫካውን፣ ትምህርት ቤቴን፣ ጓደኞቼን በቃ ሁሉንም ነገር አስታወስኩት" ትላለች ማኒሻ።
በተለይ ምንም የተመቻቸ ነገር ከሌለበት አካባቢ ለመጡ ሰዎች እንዲህ አይነት ጉዞ ማድረግ ፈታኝ ቢሆንም ይህንን ዓላማ ይዘው ልምምድ ከጀመሩ 10 ታዳጊዎች መካከል አምስቱ ህልማቸውን ዕውን ማድረግ ችለዋል።
"በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን ስናለማምድ፤ ተማሪዎቹ እንዲሮጡ አዘዝናቸው፤ ነገር ግን እንዲቆሙ መንገራችንን እረስተነው ነበር፤ ከአንድ ሰዓት በኋላ ማኒሻን ስናያት እየሮጠች ነበር ምክንያቱም እንዲቆሙ አልነገርናቸውም" ሲል አቪናሽ ዲኦስካር የተባለ አሰልጣኟ ጥንካሬዋን ያስታውሳል።
ኤቨረስት ከባህር ወለል በላይ 8,848 ሜትር ከፍታ ያለው የአለማችን ትልቁና ረጂሙን ተራራ ለመውጣት አስቸጋሪ የሆነ አደገኛ ተራራ ነው።
ከሁለት መቶ የሚበልጡ ሰዎች ተራራውን ሲወጡ ህይወታቸው አልፏል።
ራስን እንኳን ለማዘጋጀት ወራቶችን ይጠይቃል።
ታዳጊዎቹ ብርታቱን ያገኙት በ13 አመቷ ተራራውን በመውጣት በእድሜ ትንሿ ህንዳዊ ተራራ ወጭ ማላቫት ፖኦርናን ካዩ በኋላ ነበር ።
"በስህተት የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ፤ ወድቆ መፈጥፈጥ ማለት ነው" ይላል ሌላኛው ታዳጊ ፕራመሽ
ሌላኛው ታዳጊ ቪቫ ተራራውን ለሁለተኛ ጊዜ እንደወጣ ገልፆ "ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ሆነን ስንወጣ ወደቀ፤ በጊዜው ተራራውን ወጥተን 21,000 ጫማ ከፍታ ላይ እንገኝ ነበር፤ ከዚያም ተመልሼ ወደ እርሱ ወረድኩ፤ ባልደርስለት ሊሞት ይችል ነበር" ይላል ከዚህ ቀደም ተራራውን ለመውጣት ያደረገውን ሙከራ ሲያስታውስ
ይሁን እንጂ ተስፋ ሳይቆርጥ በድጋሜ ተራራውን ሊወጣ እንደቻለ ይናገራል።
በርካታ ተራራ ወጭዎች በኔፓል አቅራቢያ ባለው የተራራ ክፍል መውጣትን ይመርጣሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የሚነፍሰው ሃይለኛ ነፋስ ጋብ ስለሚል ፀደይ ወቅትን ተመራጭ ያደርጉታል።
በዚህ ወቅትም 300 ለሚሆኑ ሰዎች የተራራ መውጫ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።
ክፍያውም የሚቀመስ አይደለም፤ ለአንድ ጊዜ ፈቃድ ለመጠየቅ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ያስከፍላል።
የእነዚህ ታዳጊዎችን ህልም እውን ለማድረግ የአካባቢው አስተዳዳሪ 570 ሺ ዶላር መድቦላቸው እንደነበር የአካባቢው ባለስልጣን የሆኑት አሸስቶሽ ሳሊል ገልፀዋል።
"ሌሎች ታዳጊዎችን ለማበረታታትና በራስ መተማመን እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥሩ መንገድ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
እነዚህ ተራራውን በመውጣት በስኬት ያጠናቀቁት አምስቱ ታዳጊዎች 36 ሺህ ዶላር ሽልማት አግኝተዋል።
ታዳጊዎቹ ሌላ ተራራ የመውጣት ህልም እንዳላቸውም ተናግረዋል፤ ምናልባትም ኪሊማንጃሮን