በምዕራብ ጎጃም ታራሚ አስገድዶ የደፈረው ፓሊስ የእስራት ጊዜ ተጨመረበት

ለእስር የተዳረገችው ጓደኛዋ 'በአደራ የሰጠኋትን እቃ ሰውራለች' በማለቷ ተጠርጥራ ነው፡፡ ጉዳዩ እስከሚጣራ በአዴት ፖሊስ ጣቢያ እንድትቆይ ይደረጋል፡፡

"በጊዜው ሴት እስረኛ እሷ ብቻ ነበረች" ይላሉ የአዴት ከተማ አስተዳዳር ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ባለሙያ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር መልካሙ ወርቁ፡፡

አንድ ምሽት ያላሰበችው ሆነ፡፡

ተረኛ ጥበቃ የነበረ ፖሊስ ይህችን በህግ ከለላ ስር የነበረች ወጣት በር ከፍቶ በግድ እንድትወጣ በማድረግ፣ በመሳሪያ በማስፈራራትና በመደብደብ በጥበቃ ማደሪያ ክፍል ውስጥ አስገድዶ ደፈራት፡፡

አቤቱታ አሰማች። ከጎን ታስረው የነበሩ ወንድ እስረኞችም ሌሊት ላይ በር ሲከፈት ሰምተናል ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡

ክስ ተመሰረተ፡፡

ጉዳዩን ግራና ቀኝ አይቻለሁ ያለው የወረዳው ፍርድ ቤት ተጠርጣሪው ላይ ሁለት ዓመት ከሶስት ወር እስር አስተላለፈ፡፡

ውሳኔውም በርካቶችን አስቆጣ፡፡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነ። ፍርድ ተጓደለ ተባለ፡፡

የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጆሮ እንዴት ደረሰ?

የፍርድ ውሳኔው በወረዳው ፍርድ ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ ይፋ ከተደረገ በኋላ መስማታቸውን የማህበሩ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሜሮን አራጋው ይናገራሉ፡፡

የማህበሩ የባህር ዳር ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ፍርድ ቤቱንና ክሱን ይከታተሉ የነበሩትን አቃቤ ህግ በማነጋገር ክትትሉን ጀመረ፡፡

ወ/ሮ ሜሮን "ወጣቷ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተፈጽሞባት ሳለ ፍርድ ቤቱ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የግብረ ስጋ ግንኙነትን በተመለከተ የሚያስረዳውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 213ን ጠቅሶ ውሳኔ ማሳለፉ ጥያቄ ፈጠረብን" ይላሉ።

በወቅቱ የተጠርጣሪውን የመከላከያ ምስክር ሳይሰማና፣ የተጠቂዋን የህክምና ማስረጃ ሳያይ ብይን መስጠቱ ፍርዱ እንዲዛባ አድርጓል ይላሉ፡፡

ስለዚህም ማህበሩ ክትትሉን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡

ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ተባለ። መዝገቡ ይታይበት ወደነበረው ፍርድ ቤት ተመልሶ በድጋሚ እንዲታይም ተወሰነ፡፡

በወረዳው ፍርድ ቤት ሲታይ የቆየው ይሄው የክስ መዝገብ ሰኔ 16፣ 2010 ዓ. ም. ስምንት ዓመት ከአምስት ወር እስር በተከሳሹ ላይ ወሰነ፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንትን ጨምሮ ሌሎች ዳኞች ትብብር በማድረጋቸው የእሷን ጉዳይ በተመለከተ ይህ ነው የሚሉት ተግዳሮት እንዳልገጠማቸው ገልጸዋል፡፡

ይግባኝ?

የፍርድ ውሳኔው ይሻሻል እንጂ አሁንም ፋይሉ አልተዘጋም የሚሉት ዳይሬክተሯ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያሳልፍ የተከተላቸው የክስ ማቅለያና ማክበጃ ምክንያቶች፣ ያየው ማስረጃ፣ የቀረበበት ጊዜም ወሳኝነት ስላለው ይህንን የሚያጣራ ባለሙያ ወደ ስፍራው እንደላኩ ይናገራሉ፡፡

"አሁንም የህግ ክፍተት ካገኘንበት ይግባኝ ከማለት የሚያግደን ምክንያት የለም" ይላሉ ፡፡

ማህበራዊ ድረገጾች

ማህበራዊ ሚዲያ ትክክለኛ መረጃን መሰረት በማድረግ በአዎንታዊና በሃላፊነት መጠቀም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል ያለውን አስተዋጽኦ ጥቃቱ የተፈጸመባትን ወጣት ጉዳይ የሰሙበትን አጋጣሚ ለአብነት በማንሳት ያስረዳሉ፡፡

መረጃ ለመለዋወጥ፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለማውጣትና ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ ብሎም ማስረጃዎች ቅርብ እንዲሆኑ ለማድረግ የማህበራዊ ድረ ገጾችን አስፈላጊነትን ያነሳሉ፡፡

የማህበሩ ተግዳሮቶች

ማህበሩ በስድስት የክልል ከተሞች ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ያሉት ሲሆን 53 ማዕከላትም አሉት ፡፡

ማህበሩ በተለያየ ጊዜ በሴቶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን አደባባይ በማውጣትና ለህግ በማድረስ ፍትህ እንዲያገኙ አስችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጣው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ ባሰቡት መጠን ስራቸውን እንዳይሰሩ እየተፈታተናቸው እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

"ህጉ በመሻሻል ሂደት ላይ በመሆኑ ፈተናችን ይቀየራል የሚል ተስፋ አለኝ" ብለውናል ዳይሬክተሯ፡፡

ማህበሩ በዓመት 10,000 የሚሆኑ ኬዞችን ይቀበላል፡፡ ከእነዚህ መካከል 1,000 የሚሆነው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ነው፡፡