ግርማዊት ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤጥ

የፎቶው ባለመብት, Yousuf Karsh / Camera Press
ረጅሙ የንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ ዘመነ ንግሥና ጠንካራ በሆነ የኃላፊነት መንፈስ እንዲሁም ሕይወታቸውን ለዘውድ እና ለሕዝባቸው ሙሉ በሙሉ በመስጠት የሚገለፅ ነው።
ነገሮች ከባድ በነበሩባቸው ጊዜያት ዘውዳዊውን ሥርዓት አስጠብቀው በማቆየት ረገድ ያስመዘገቡት ስኬት የበለጠ አስደናቂ የሚሆነው ሲወለዱ ማንም ዙፋኑ አንድ ቀን የእርሳቸው እንደሚሆን ገምቶ እንደማያውቅ ሲታሰብ ነው።
ኤልዛቤት አሌክሳንድራ ሜሪ ዊንድሰር የተወለዱት በለንደን ከተማ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 21 ቀን 1926 ነው። የዮርክ መስፍን የነበሩት የአልበርት እና የባለቤታቸው የቀድሞዋ እመቤት ኤልሳቤጥ ባዎስ-ሊዮን የበኩር ልጅ ነበሩ። የአባታቸው የንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ፤ ሁለተኛ ልጅ ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤልዛቤጥ እና እ.ኤ.አ በ1930 የተወለዱት እህታቸው ማርጋሬት ሮዝ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በቤት ውስጥ ነው።
ከሌሎች የዕድሜ እኩዮቻቸው ታዳጊ ልጃገረዶች ጋር ወዳጅነት እንዲፈጥሩ እና አብረው ጊዜ እንዲያሳልፉም በማሰብ የዓለም አቀፉ የስካውት እንቅስቃሴ ቅርንጫፍ የሆነ የልጃገረድ መሪዎች ቡድን በባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ውስጥ ተመስርቶላቸው ነበር።
ኤልዛቤጥ ገና ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ የኃላፊነት ስሜትን ያንፀባርቁ እንደነበር ይነገራል።
በኋላ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዊንስተን ቸርችል "በሕፃናት ላይ ሲታይ እጅግ የሚገርም የሆነ የሥልጣን ስሜት" መላበሳቸውን እንደተናገሩላቸውም ይጠቀሳል።
የውጥረት መጨመር
ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ እ.ኤ.አ በ1936 መሞታቸውን ተከትሎ የበኩር ልጃቸው ዴቪድ የንግሥና ስማቸውን ኤድዋርድ ስምንተኛ አድርገው ነገሡ።
ይሁንና ንጉሡ የመረጧቸው ሁለተኛ ሚስታቸው፤ ሁለት ጊዜ አግብተው የፈቱት አሜሪካዊቷ ዋሊስ ሲምሰን ስለነበሩ እርሳቸው በፖለቲካዊ እና ኃይማኖታዊ ምክንያቶች ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም። በዓመቱ መጨረሻ ላይም ንግሥናቸውን ተዉት።
ታናሽ ወንድማቸው የዮርኩ መስፍን ቸል እያሉም ቢሆን ንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ ተብለው ንግሥናውን ተረከቡ።
በአውሮፓ የፖለቲካ ውጥረት እየገነነ በነበረበት በዚያ ወቅት አዲሱ ንጉሥ ከሚስታቸው ኤልሳቤጥ ጋር ህዝቡ በዘውዳዊው ሥርዓት የነበረውን እምነት ዳግም ለመገንባት ታጥቀው ተነሱ።
ይህን ምሳሌያቸውን ታላቋ ልጃቸው ኤልሳቤጥ መከተሏ አልቀረም።
በ1939 የአስራ ሦስት ዓመቷ ልዕልት ወላጆቻቸው ንጉሡን እና ንግሥቲቷን ተከተለው ዘውዳዊውን የባሕር ኃይል ኮሌጅ ለመጎብኘት ሄዱ።
ከእህታቸው ከማርጋሬት ጋር ታዳጊዋ ልዕልት ከእጩ መኮንኖቹ የሩቅ ዘመዳቸው በሆኑት በአንደኛው የግሪኩ ልዑል ፊሊፕ ታጅበው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንቅፋቶች
ሲገናኙ የመጀመሪያቸው አልነበረም፤ ሆኖም ልዕልቲቷ በልዑሉ ላይ ፍላጎት ሲያሳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ልዑል ፊሊፕ ከባሕር ኃይሉ እረፍት ላይ በነበሩበት ጊዜ ንጉሣዊ ዘመዶቻቸውን ጎበኙ።
በ1944 የአስራ ስምንት ዓመቷ ኤልሳቤጥ ከልዑሉ ጋር በፍቅር እንደወደቁ ግልፅ ሆነ።
ጦርነቱ ወደመገባደጃው ሲቃረብ፤ ወጣቷ ልዕልት "ደጋፊ የድንበር አግልግሎት"ን ተቀላቅለው የጭነት መኪና መንዳትና መጠገንን ተማሩ።
ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ልዑል ፊሊፕን ለማግባት የነበራቸው ፍላጎት በበርካት ነገሮች ተደነቃቀፈ።
ንጉሡ በጣም የሚወዷትን ሴት ልጃቸውን አሳልፈው ለመስጠት፤ የፊሊፕ የዘር ሐረግ ከውጭ ሃገር የሚመዘዝ በመሆኑ በመኳንንቱ ዘንድ የሚታየውን መገለል መቋቋም ነበረባቸው።

የፎቶው ባለመብት, PA
የአባት ሞት
ሆኖም የጥንዶቹ ምኞት የኋላ ኋላ ሰምሮ 1947 በዌስትሚኒስትር አቢ ተጋቡ።
ይህን ተከትሎ የኤደንብራ መስፍን የሆኑት ፊሊፕ የባሕር ኃይል መስሪያ ቤትን እያገለገሉ ቆዩ። ልዑሉ በማልታ ሲመደቡ ቢያንስ ለአጭር ጊዜ ጥንዶቹ በአንፃራዊነት መደበኛ የሆነ ህይወትን መርተዋል።
የበኩር ልጃቸው ቻርልስ በ1948 የተወለዱ ሲሆን እህታቸው አን ደግሞ በ1950 ይህችን ዓለም ተቀላቅለዋል።
ነገር ግን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ጫና የነበረባቸው ንጉሡ፤ ከሲጋራ ጋር የተያያዘ የሳንባ ካንሰር በሽታ ተጠቂ ሆኑ።
በ1952 ያን ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ወጣት የነበሩት ኤልሳቤጥ እና ባለቤታቸው ፊሊፕ የተለያዩ ውጪ አገራትን መጎብኘት ጀመሩ።
ኬንያ ውስጥ እንዳሉም ኤልሳቤጥ የአባታቸውን ሞት ሰሙ፤ ወዲያውኑም ወደለንደን ተመልሰው አዲሲቷ ንግሥት ለመሆን በቁ።
አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ
በሰኔ 1953 የተከናወነው በዓለ ንግሥናቸው በቴሌቭዥን በቀጥታ የተላለፈ ሲሆን ሚሊዮኖች ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ቃለ መሃላ ሲፈፅሙ ተከታትለዋል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የብሪታንያን የአፄ ሥርዓት አጠናክሮታል፤ እናም አዲሲቷ ንግሥት በ1953 ወደ ብሪታንያ የጋራ ብልፅግና (ኮመንዌልዝ) አገራት ጉብኝት ሲያቀኑ በርካታ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች ነፃነታቸውን አግኝተው ነበር።
ኤልሳቤጥ በንግሥና ላይ ሳሉ አውስትራሊያን እና ኒውዚላንድን የጎበኙ የመጀመሪያዋ ንግሥት ሆነዋል። በወቅቱም ከአውስትራሊያዊያን መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት በአካል እንዳዩዋቸው ይገመታል።
በ1950ዎቹ በጠቅላላ በርካታ አገራት የብሪታንያ የአፄ ሥርዓት ግዛትን ሰንደቅ ዓላማ ቢያወርዱም ብዙ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች በፈቃደኛነት ቤተሰብ አገራት ወደመሆን ተቀይረዋል።
በርካታ ፖለቲከኞች አዲሱ ኮመንዌልዝ ብቅ እያለ ለነበረው የአውሮፓ የምጣኔ ኃብት ማኅበረሰብ መመከቻ ነው የሚል ስሜት አንፀባርቀዋል።
የ1956ቱ የስዊዝ መተላለፊያ ቦይ ቀውስ የብሪታንያ ተፅዕኖ መዳከምን አፋጥኗል።
ግብፅ የስዊዝ መተላለፊያን ብሔራዊ ንብረት አድርጋ ልትወርሰው እንደሆነ ስትዝት የብሪታንያን ጦር ለመላክ መወሰኑና እርምጃው በሚያሳፍር ማፈግፈግ ተደምድሟል።
ይህም የጠቅላይ ሚኒስትር አንተኒ ኤድንን ከስልጣን መልቀቅንም አስከትሏል።

የፎቶው ባለመብት, PA
ማዘመን
በ1960ዎቹ መገባደጃ ንጉሣዊውን ቤተሰብ ቀለል ባሉ እና ከተራ ሕዝብ ጋር በሚያቀራርቡ ሁኔታዎች ውስጥ ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ወሰነ።
የዚህም ፈር ቀዳጅ የሆነው "ሮያል ፋሚሊ" የሚል ርዕስ ያለው ዘጋቢ ፊልም ሆነ። ፊልሙ የተሠራው ቢቢሲ የዊንድሰርን ቤተሰብ በቤታቸው ውስጥ እንዲቀርፅ ተፈቅዶለት ነው ።
በፊልሙ የንጉሣዊው ቤተሰብ አባላት ሥጋ በመጥበስ ላይ፣ የገና ዛፍን ሲያሸበርቁ፣ ልጆችን በመኪና ሽርሽር ሲወስዱና ሌሎች ዓይነት ተራ እንቅስቃሴዎች ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ምስሎች ናቸው።
በ1977 ንግሥቲቷ ለሃያ አምስት ዓመት ዘውዳዊውን ሥርዓት የመሩበት የብር ኢዮቤልዮ በድምቀት ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ዘውዳዊው ሥርዓት አስተማማኝ የሕዝብ ፍቅር ማትረፍ መቻሉ የተስተዋለ ሲሆን ይህም ባመዛኙ የንግሥቲቷ ውጤት ነበር።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ብሪታንያ የመጀመሪያዋን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸርን አገኘች።
በእንስቷ ርዕሰ-ብሔር እና በእንስቷ ርዕሰ-መንግሥት መካከል የነበረው ግንኙነት አንዳንዴ ውጥረት የሞላበት እንደነበር ይነገራል።
አንደኛው አስቸጋሪ ነገር ንግሥቲቷ የበላይ ለሆኑበት የጋራ ብልፅግና ሃገራት ማኅበር ያላቸው አመለካከት ነበር። ኤልሳቤጥ የአፍሪካ መሪዎችን ያውቋቸው ስለነበር መሪዎቹ ለሚታገሉላቸው ዓላማዎችም አዛኝ ነበሩ።
የታቸር አቀራረብ እና ተጋፋጭ የሆነ አሰራር ለኤልሳቤጥ "እንቆቅልሽ" የሆነባቸው ሲሆን፤ በተለይም ታቸር የደቡብ አፍሪካውን የአፓርታይድ ሥርዓት በመቃወም ማዕቀብ ለመጣል ያለመፈለጋቸው አንዱ ያለመግባባት ምንጭ ነበር።
በ1991 የባሕረ-ሠላጤው ጦርነት ወቅት ዩናይትድ ኪንግደም ዩናይትድ ስቴትስን ደግፋ ኩዌትን ከኢራቅ በምትከላከልበት ወቅት ንግሥት ኤልሳቤጥ ወደ አሜሪካ አቀኑ።
በዚህም ለአሜሪካን የህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች በጥምር ንግግር ያደረጉ የመጀመሪያዋ የብሪታንያ ንጉሣዊ መሪ ሆነዋል። ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ቡሽ ንግሥቲቷን "እስከምናስታወሰው ጊዜ ድረስ የነፃነት ወዳጅ" ናቸው ብለዋቸዋል።
ቅሌቶች
ይሁንና ከአንድ ዓመት በኋላ ተከታታይ ቅሌቶች እና ቀውሶች ንጉሣዊውን ቤተሰብ ያናውጡት ገቡ።
የንግሥቲቷ ሁለተኛ ልጅ የዮርኩ መስፍን እና ሚስታቸው ሳራ ሲለያዩ፣ ልዕልት አን ከማርክ ፊሊፕስ ጋር የነበራቸው ትዳር በፍች ተጠናቅቋል።
ከዚያም የዌልሱ ልዑል እና ሚስታቸው ልዕልት ዳያና እጅጉን በትዳራቸው ደስተኛ ያለመሆናቸውን አሳውቀው የኋላ ኋላም ተለያዩ።
ዓመቱ የተጠናቀቀው ንግሥቲቷ ከመኖሪያዎቻቸው ሁሉ አብልጠው በሚወዱት በዊንድሰር ቤተ-መንግሥት በተነሳ ግዙፍ እሳት ነው። እሳቱ ነውጥ ውስጥ ለነበረው ንጉሣዊ ቤተሰብ የሚስማማ ትዕምርት ይመስል ነበር።
እርሱን ተከትሎ ቤተ-መንግሥቱን ለማስጠገን የሚውለውን ወጪ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ነው መሸፈን ያለበት ወይንስ ንግሥቲቷ ራሳቸው ናቸው በሚል የተነሳው ጭቅጭቅም ነገሩን አጦዘው።
1992 መጥፎው ዓመታቸው መሆኑን ገልፀው የነበረ ሲሆን የመገናኛ ብዙኃን የሚሰነዝሩትን ትችት ለመቀነስ የበለጠ ግልፅ የሆነ ዘውዳዊ አስተዳደርን መገንባት እንደሚያስፈልግም ያመኑ መስለው ነበር።
የዊንድሰርን ጥገና ወጪ ለመሸፈን ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ለጎብኝዎች ክፍት ሲሆን፤ ንግሥቲቷ እና የዌልሱ ልዑል በኢንቨስትመንት ገቢያቸው ላይ ግብር እንደሚከፍሉም አሳውቀዋል።
በንግሥና ዘመናቸው መባቻ ዓመታት ከፍተኛ የነበረውና ለጋራ ብልፅግና ሃገራት ማኅበር የሰነቁት ተስፋ ሳይሟላ ቀርቷል። ብሪታንያ አዲሱን የአውሮፓ መዋቅር ተቀብላ የቀድሞ አጋሮቿ ላይ ፊቷን አዞረች።
እንዲያም ሆኖ ግን ንግሥቲቷ የጋራ ብልፅግና ሃገራት ማኅበር ፋይዳ ከፍ ብሎ ስለሚታያቸው ደቡብ አፍሪካ አፓርታይድን ስትጥል የተሰማቸውን ደስታ ያከበሩት 1995 ላይ ደቡብ አፍሪካን በመጎብኘት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዌልሷ ልዕልት ዳያና ሞት
በ1997 የዌልሷ ልዕልት ዳያና ፓሪስ ውስጥ በመኪና አደጋ ሲሞቱ ዘውዳዊው ቤተሰብ እንደገና ተናወጠ። ንግሥቲቷ ራሳቸውም ያልተለመደ ዓይነት ነቀፌታ ዘነበባቸው።
ሕዝቡ የመታሰቢያ አበባ ይዞ ለንደን ውስጥ ባሉት የንጉሣዊያኑ መቀመጫ ሲሰባሰብ፤ ንግሥቲቷ ታላላቅ ብሔራዊ ክስተቶች በሚኖሩበት ወቅት ሁሌም ያደርጉት የነበረውን ዓይነት አትኩሮት ለመስጠት ቸልተኛ የሆኑ መሰሉ።
የኋላ ኋላ በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ ንግግር አድርገዋል። በዚህም የልጃቸውን ሚስት ሲዘክሩ ንጉሣዊው ቤተሰብ ችግሩን ተቋቁሞ እንደሚዘልቅም አስረግጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA
ህልፈትና እና ክብረ በዓሎች
የንግሥቲቷ እናት እና ልዕልት ማርጋሬት በ2002 መሞታቸው ንግሥቲቷ ለሃምሳ ዓመታት ያህል በንግሥና የቆዩበትን የወርቅ ኢዮቤልዩ ለማክበር በተሰናዳው ሃገር አቀፍ ዝግጅት ላይ ጥላውን አሳረፈ።
ነገር ግን ከዚህ በተፃራሪ የዘውዳዊው ሥርዓትን መፃኢ ዕጣ አስመልክቶ በተዘጋጀ ክርክር ላይ ከባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ፊት ለፊት ባለው ዘ ሞል የተሰኘ ጎዳና አንድ ሚሊዮን ሰዎች የኢዮቤልዩው ክብረ በዐል ላይ ታድመው ነበር።
በ2007 ንግሥቲቷ እና ልዑል ፊሊፕ የጋብቻቸውን 60ኛ ዓመት ሲያከብሩ፣ በሚያዝያ 2011 ደግሞ የልጅ ልጃቸውን የካምብሪጁን መስፍን የዊሊያም እና የካትሪን ሚድልተንን ሠርግ ታድመዋል።
በ2012 ኤልሳቤጥ ንግሥት የሆኑበት ስድሳኛ ዓመት ለሚዘከርበት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መሰናዶ ተጨማሪ ክብረ በዐል ነበር።
በ2014 ስኮትላንድ ነፃ መውጣት ያለመውጣትን ለመወሰን ያደረገችው ሕዝበ-ውሳኔ ለንግሥቲቷ ፈታኝ ጊዜ ነበር።
ስኮትላንድ በጠባብ ልዩነት የዩናይትድ ኪንግደም አካል ሆና ለመቀጠል የመወሰኗ ውጤት ሲታወቅ፤ ንግሥቲቷ ለሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት ዩናይትድ ኪንግደም አሁንም አንድ ሆና መቀጠሏ የፈጠረባቸውን እፎይታ የሚያስረግጥ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, PA
በ2015 በብሪታንያ ታሪክ ረጅም ዘመን በንግሥና መንበራቸው ላይ የቆዩት ዘውዳዊ መሪ ሆኑ። ይህንንም ያሳኩት የአያታቸውን አያት ንግሥት ቪክቶሪያን በንግሥና በቆዩበት ጊዜ በመብለጥ ነበር።
ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ደግሞ በሚያዝያ 2016 የዘጠናኛ ዓመት ልደታቸውን፣ በሕዳር ወር 2017 ደግሞ ከፊሊፕ ጋር የተጋቡበትን 70ኛ ዓመት አከበሩ።
ምንም እንኳ ንጉሣዊው ሥርዓት እሳቸው ሲነግሡ የነበረውን ያህል ጥንካሬ በንግሥናቸው መደምደሚያ ላይ ባይኖረውም፤ በብሪታንያዊያን ዘንድ የፍቅር እና የክብር ቦታ ሆኖ መዝለቅ እንዳለበት ጠንካራ እምነት ነበራቸው።
የብር ኢዮቤልዩዋቸውን ሲያከብሩ ከሰላሳ ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ ባቀኑበት ወቅት የገቡትን ቃል አስታውሰው ነበር፤
"የሃያ አንድ ዓመት ወጣት ሳለሁ ህይወቴን ለሕዝባችን ግልጋሎት ለማዋል ቃል ገብቻለሁ። ይህንን ቃል ጠብቄ እንድኖርም የእግዚያብሔርን እርዳታ ጠይቄያለሁ። ምንም እንኳ ያ ቃል የተገባው ጮርቃ በነበርኩበት በለጋነት ዕድሜዬ ቢሆንም፤ አንዲቷም ቃል አትቆጨኝም፣ አንድም ቃል ልቀንስበትም አልሻም።"












